የዩጋንዳ አገራዊ ምርጫ ሊካሄድ ሁለት ቀናት ብቻ ሲቀሩት የሙሴቪኒ መንግስት በአገር አቀፍ ደረጃ የኢንተርት አገልግሎትን አቋርጧል።
እርምጃው የተወሰደው በምርጫው እለት ሊፈጠር የሚችል የተዛባ መረጃ ስርጭት እና አመጽ ቅስቀሳን ለማስቀረት በማሰብ እንደሆነ የዩጋንዳ ኮሚኒኬሽን ኮሚሽን (UCC) አስታውቋል።
እገዳው ከዛሬ ማክሰኞ ጀምሮ የተተገበረ ሲሆን፥ ላልተወሰነ ግዜ እንደተቋረጠ እንደሚቆይ ኮሚሽኑ አስታውቋል። የመደበኛ ሞባይል ዳታ ቢቋረጥም ትልልቅ ሆቴሎች እና መሰል የቢዝነስ ተቋማት አገልግሎት መቀጠላቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
በዜጎች ሕይወት ላይ የሚኖረው ተጽዕኖ
የኢንተርኔት መዘጋቱ ከመረጃ ልውውጥ ባለፈ በዩጋንዳውያን የዕለት ተዕለት ኑሮ ላይ ከፍተኛ ጫና ይፈጥራል። በተለይም በሀገሪቱ በስፋት የሚተገበረው የሞባይል ገንዘብ ክፍያ (Mobile Money) መቋረጡ ንግድና ማህበራዊ ግንኙነቶችን ሽባ እንደሚያደርግ ስጋት ተፈጥሯል። መንግሥት በተጨማሪም አንዳንድ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ሥራቸውን እንዲያቆሙ ማስጠንቀቂያ መላኩ በቀጣዩ ምርጫ ላይ ጥርጣሬዎችን አሳድሯል።
እንደ ሮይተርስ ዘገባ፥ የምርጫውን መቃረብ ተከትሎ የዩጋንዳ መንግስት ለአንዳንድ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች እና መንግታዊ ያልሆኑ ተቋማት፥ ስራቸውን እንዲያቋርጡ የማሳሰቢያ ደብዳቤዎችን ልኳል።
የ81 አመቱ ዩዌሪ ሙሴቪኒ፥ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ለአራት አስርት አመታት በተከታታይ በስልጣን የቆዩ ሲሆን በዚህ ዙር ለስልጣን ሲወዳደሩ ሰባተኛቸው ነው። ፕሬዝደንቱ ሁለት ግዜ ህገ-መንግስታቸውን በማሻሻል የስልጣን እድሜ ጣሪያውን ያራዘሙ ሲሆን በአፍሪካ ለረዥም አመታት በስልጣን ላይ ከቆዩ መሪዎች ከቀዳሚዎቹ ጎራ ተቀምጠዋል።
ዋናው የሙሴቪኒ ተቃዋሚ ቦቢ ዋይን ለምርጫው ውድድር ከቀረቡት መሃል የተሻለ ግምት የተሰጠው እጩ ሆኗል።











