የኢትዮጵያ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን በተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎችን ለማሰብ ለሶስት ቀናት የሚቆይ ብሔራዊ ሀዘን መታወጁን በዛሬው እለት አስታውቋል።
መጋቢት 2፣ 2018 ዓ.ም በዞኑ በጋጫ ባባ ወረዳ ላቃ ቀበሌ የተከሰተው ይህ የመሬት መንሸራተት አደጋ በአካባቢው የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ የመጣ መሆኑን የክሎሉና የዞኑ ባለስልጣናት እየተናገሩ ናቸው።
የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ በትናንትናው እለት ባወጣው መረጃ የሟቾች ቁጥር 70 መደረሱን፣ 190 ቤቶች መውደማቸውን ከ3000 በላይ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውንም ጠቅሶ ነበር።
ነገርግን የተወካዮች ምክርቤት ባወጣው መግለጫ በአደጋው የሞቱ ሰዎች ቁጥር 80 ሲደርስ ሌሎች 45 ሰዎች የደረሱበት አልታወቀም።
አዋጁ ከነገ ጀመሮ እስከ ሰኞ ድረስ እንደሚቀጥል የገለጸው ምክርቤቱ፣ በእነዚህ የሀዘን ቀናት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሰንደቅ አላማ በመንግስት ተቋማትና በኤምባሲዎች ቅጥር ግቢ ዝቅ ብሎ ይውለበለባል ብሏል።
በአሁኑ ወቅት መንግስት አደጋው በተከሰተበት ቦታ የነፍስ አድን ስራ እየሰራ መሆኑንም መግለጫው ጠቅሷል።
በክልሉ ከባድ ዝናብን ተከትሎ የመሬት መንሸራተትና የጎርፍ አደጋዎች በተደጋጋሚ ይከሰታሉ። ከሁለት አመት በፊት በክልሉ ጎፋ ዞን በተከሰተ ከባድ የመሬት መንሸራተት አደጋ ከ200 በላይ ሰዎች መሞታቸውን ይታወሳል።












