በኬንያ በመካከለኛው ምስራቅ በተቀሰቀሰው ጦርነት ምንክያት የተፈጠረው የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ቁጣ የቀላቀለ ተቃውሞ ተቀስቅሷል።
የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች አድማ በመምታታቸው ምክንያት ተጓዦች ባሉበት ለመቆም ተገደዋል።
የኬንያ የሀገር ውስጥ ሚኒስቴር እንደገለጸው በተቃውሞው እስካሁን አራት ሰዎች ተገድለዋል። የትራንስፖርት ዘርፍ አሊያንስ በትናንትናው እለት የማህበር አባል የሆኑ ተሽከርካሪዎች ከእኩለ ሌሊት ጀምረው እንደሚያቆሙ ሲያስታውቅ ፖሊስ በበኩሉ ምንም አይነት መስተጓጐል እንዳይፈጠር መንቀሳቀስ እንዳለባቸው አስጠንቅቆ ነበር።
“በዛሬው አመጽ አራት ኬንያውያንን አጥተናል” ሲሉ የሀገር ውስጥ ሚኒስትሩ ኪፕቹምባ ሙርኮሜን ተናግረዋል።
የኬንያ የኃይልና የፔትሮሊየም ቁጥጥር ባለስልጣን ባለፈው ሳምንት የነዳጅ ችርቻሮ መሸጫ ዋጋን በ23.5 በመቶ ከፍ አድርጓል። ባለስልጣኑ ይህን ጭማሪ ያደረገው የ24.2 በመቶ ጭማሪ ካደረገ ከወር በኋላ ነው።
ከሰኞ ጠዋት ጀምሮ ወደ ዋና ከተማዋ ናይሮቢ የሚወስዱ መንገዶች ተቃውሞ በሚያሰሙ አሽከርካሪዎች በመዘጋታቸው፣ የትራፊክ ፍሰቱ የበለጠ እንዲጨናነቅና ተጓዦች እንዳይንቀሳቀሱ አድረጓል።
ፖለሲ በአንዳንድ ቦታዎች የአስለቃሽ ጭስ ቦንብ የተኮሰ ሲሆን የተወሰኑ ሰልፈኞች ደግሞ ጎማ በማቃጠል መንገዱን ዘግተዋል።
በተለይ በኬንያዋ የወደብ ከተማ ሞምባሳ የተቀሰቀሰው ተቃውም የአቅርቦት መስተጓጎልን እንዳያስከትል ተሰግቷል።ሙርኮሜን እንደገለጹት የፋይናንስ፣ የትራንስፖርትና የኃይል ሚኒስትሮች ችግሩን ለመፍታት ከአሸከርካሪዎች ጋር ተወያይተዋል።
ኬንያ ሙሉ የነዳጅ ፍጆታዋን ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ጋር በሚደረግ የመንግስት ለመንግስት ስምምነት ነው።












