የምስራቅ ሊቢያ መንግስት የኢትዮጵያ፣ የኤርትራ፣ የሶማሊያና የሱዳን ዜጎች ወደ ግዛቱ እንዳይገቡ ከባለፈው ማክሰኞ ጀምሮ እግድ መጣሉን አስታውቋል።
እንደ ሮይተርስ ዘገባ ከሆነ በሀገሪቱ ሁለተኛ ትልቅ ከተማ በሆነችው ቤንጋዚ መቀመጫውን ያደረገው ይህ ትይዩ መንግስት ከእነዚህ ሀገራት የሚመጡ ዜጎች”በመሬት፣ በአየርና በባህር” ወደሚያስተዳድረው የሀገሪቱ ክፍል እንዳይገቡ ወስኗል። መቀመጫውን ቤንጋዚ ያደረገው መንግስት፣ የምስራቅ ሊቢያንና ሰፊውን ደቡባዊ የሊቢያ ክፍልን የሚቆጣጠረው ወታደራዊ መሪ ከሊፋ ኻፍታር አጋር ነው።
በተመድ ድጋፍ እአአ በ2021 ወደ ስልጣን የመጣውና አለምአቀፍ እውቅና ያለው በአብዱልሃሚድ ድበይባህ የሚመራው መንግስት ደግሞ መቀመጫውን በዋና ከተማዋ ትሪፖሊ አድርጓል።
ሮይተርስ የምስራቅ ሊቢያ መንግስት ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው ውሳኔው የተላለፈው የሚገቡ የውጭ ዜጎችን ለማደራጀት በማለም ነው። ይህ ውሳኔ፣ እግድ ከተጣለባቸው ሀገራት የሚመጡ ዲፕሎማቶችን፣ የቆንስላ ስራተኞችን እንዲሁም ቤተሰቦቻቸውን አያካትትም ተብሏል። ከዚህ በተጨማሪም በትምህርት፣በጤና እና ተያያዥ የጤና አገልግሎት ዘርፍ ያሉ ሰራተኞች ከሚመለከታቸው አካላት ህጋዊ የስራ ውል እንደሚሰጣቸው ተገልጿል።
ሊቢያን ለረጅም ጊዜ የመሩት ሙአማር ጋዳፊ እአአ በ2011 ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ ሀገሪቱ ድህነትና ጦርነትን ሸሽተው የሜዲትራንያን ባህር አቋርጠው ወደ አውሮፓ ለሚያቀኑ ስደተኞች ዋነኛ መሸጋገሪያ ሆና እያገለገለች ትገኛለች። ከአመት በፊት የወጣው የተመድ መረጃ እንደሚያሳየው ሊቢያ ከ900,000 በላይ ስተደኞችን አስጠልላለች።













