የቀድሞው የኢትዮጵያ አየርመንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ የነበሩት አቶ ተወልደ ገብረማሪያም የህንዱ ኤየር ኢንዲያ ዋና ስራ አስፈጻሚና ማኔጂንግ ዳሬክተር ሆነው መቀጠራቸውን ኤየር ኢንዲያ በጽረ ገጹ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ባለፈው ወር አቶ ተወልደ የፓኪስታን አለምአቀፍ አየርመንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሆነው መቀጠራቸውን የሚገልጹ የሚዲያ ዘገባዎች ወጥተው የነበረ ቢሆንም መዳረሻቸው ኤየር ኢንዲያ ሆኗል።
አቶ ተወልደ በዋና ስራ አስፈጻሚነት ሲያገለግሉ የነበሩትን ካምቤል ዊልሰንን ይተካሉ።
አየርመንገዱ እንዳስታወቀው የኤየር ኢንዲያ ቦርድ ከመላው አለም ያመለከቱ እጩዎችን በጥልቀት ከገመገመ በኋላ አቶ ተወልድ ብቁ ሆነው አግኝቷቸዋል። በግምገማው መሰረት አቶ ተወልደ ለኤየር አንዲያ የሚሆን ስትራቴጂካዊ አፈጻጸምና የአመራር አቅም እንዲሁም በዘርፉ ያላቸው ልምድ ተመራጭ ተደርገዋል።
ከአስርት አመታት በላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሆነው ያገለገሉት አቶ ተወልደ ገብረማርያም፣ በአፍሪካ በዘርፉ ስኬታማ ከሚባሉት የአቪዬሽን ሰው ተጠቃሽ ናቸው። አቶ ተወልደ የኢትዮጵያ አየርመንድ ገቢ እንዲጨምር፣ አለምአቀፍ መዳረሻዎቹና አጠቃላይ ያሉት የአውሮፕላኖች ቁጥር በሶስት እጥፍ ገደማ እንዲጨምሮ አስተዋፅኦ ማድረጋቸው ይነገርላቸዋል።










