በቱርክ፣ አንታሊያ እየተካሄደ ያለው የተባበሩት መንግሥታት COP31 የአየር ንብረት ጉባኤ ድርድር፣ አገራት በአዲስ ዓለም አቀፍ ስምምነት ላይ መግባባት ባለመቻላቸው በታቀደለት ጊዜ ሳይጠናቀቅ ቀርቷል።
ፈረንሳይና ፓናማን ጨምሮ በርካታ አገራት ዓርብ ዕለት በቀረበው የስምምነት ረቂቅ ላይ ተቃውሞ አቅርበዋል። ረቂቁ የቅሪተ አካል ነዳጆችን አጠቃቀም ለመቀነስ የሚያስችል ማጣቀሻ አለማካተቱ የድርድሩ ዋነኛ ማነቆ ሆኗል።
ሌላው የአለመግባባት ምንጭ የአፍሪካ ቡድን ለአየር ንብረት ለውጥ መላመድ የሚውል ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ እንዲመደብ ያቀረበው ጥያቄ ሲሆን፣ የአውሮፓ ሕብረት ቀደም ሲል ይህንን እንደማይደግፍ ገልጾ ነበር።
የደሴት አገራት፣ ፓናማና ስፔን፣ ፈረንሳይ፣ ቤልጂየም፣ ስዊድንና ፊንላንድን ጨምሮ የአውሮፓ ሀገራት የነዳጅ ዘይት፣ የጋዝና የድንጋይ ከሰል ጥገኝነትን ለመቀነስ የሚያስችል ቃል ኪዳን በመጨረሻው ስምምነት እንዲካተት እየጠየቁ ነው። ይህ ጥያቄ የተነሳው በሳዑዲ አረቢያ የሚመራው የነዳጅ አምራች አገራት ጉዳዩ ከረቂቁ እንዲወገድ ከጠየቁ በኋላ ነው።
የፓናማ የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትር ሁዋን ካርሎስ ናቫሮ፣ የቅሪተ አካል ነዳጆችን የማይጠቅስ የCOP ውሳኔ ተቀባይነት እንደሌለው ተናግረዋል። የፈረንሳይ የሥነ ምህዳር ሽግግር ሚኒስትር ሞኒክ ባርቡትም በተመሳሳይ የካርቦን ቀረጻና ማከማቻ ቴክኖሎጂ ዘይትና ጋዝ ማቃጠልን ለመቀጠል ሰበብ መሆን የለበትም ብለዋል።
በይፋ “የአንታሊያ ስምምነቶች” ተብሎ በተጠራው ሰነድ ውስጥ፣ የዓለምን የሙቀት መጠን ጭማሪ ከ1.5 ዲግሪ ሴልሺየስ በታች የማቆየት ግብ እንዳልተሳካ ለመጀመሪያ ጊዜ እውቅና ተሰጥቷል። ሳይንቲስቶችም በባሕር ወለል ከፍታ ጭማሪና በከፍተኛ ሙቀት ምክንያት ተጨማሪ ሚሊዮኖች ለአደጋ እንደሚጋለጡ ያስጠነቅቃሉ።
የአውስትራሊያ የአየር ንብረት ለውጥና ኢነርጂ ሚኒስትር ክሪስ ቦወን ግን ጉባኤው በተግባራዊ እርምጃዎችና ወደ ታዳሽ የኢነርጂ ምንጮች በሚደረገው ሽግግር ላይ ማተኮር እንዳለበት ገልጸዋል።
በሌላ በኩል፣ የታዳሽ ኢነርጂ አጠቃቀም በዓለም እያደገ መሆኑ ተጠቁሟል። በዚህ ዓመት የፀሐይ ኃይል የዓለምን የኢነርጂ ፍላጎት ዕድገት ከፍተኛውን ድርሻ ይዟል።
በድርድሩ ላይ እየተመረመረ ካለው ሌላ ሐሳብ፣ ሳዑዲ አረቢያና ሌሎች የነዳጅ ሀብታም አገራት እ.ኤ.አ. እስከ 2035 ድረስ 35 በመቶ የኃይል ፍጆታቸውን ከኤሌክትሪክ ለማግኘት ቃል ከገቡ፣ የቅሪተ አካል ነዳጆች ጉዳይ ከስምምነቱ እንዲወጣ የሚል ሐሳብ ቀርቧል።
ይሁንና የታዳጊ አገራት ዋነኛ ጥያቄ የሆነው የገንዘብ ድጋፍ እጥረት አሁንም አልተፈታም። ቀደም ባለው የስምምነት ረቂቅ ለአየር ንብረት ለውጥ መላመድ እስከ 2035 ድረስ 120 ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ የተያዘው ሐሳብ ከረቂቁ ተወግዷል።
የጋና የአካባቢ ሚኒስትርና የአፍሪካ ቡድን የድርድር ተወካዮች ሰብሳቢ ዛኔቶር አግየማን ራውሊንግስ፣ አፍሪካ ለመለመን ሳይሆን በባደጉ አገራት ተግባራት ምክንያት ለተጎዱ ሕዝቦቿ በመብት የሚገባቸውን ለመጠየቅ እንደመጣች ተናግረዋል።
በድርድሩ ላይ ታዛቢ የሆኑ የአየር ንብረት ተሟጋቾችና የአካባቢ ጥበቃ ቡድኖችም ሂደቱን ተችተዋል። የፓወርሼፍት አፍሪካ ዳይሬክተር መሐመድ አዶው ጉባኤውን “ከሁሉም የከፋው COP” ሲሉ ገልጸውታል።
በተጨማሪም የቱርክ ዋና የድርድር ተወካይ በአንዳንድ ወሳኝ ድርድሮች ላይ ቦታውን ለቆ መውጣቱ በርካታ አገራት እንደተናቁ እንዲሰማቸው ማድረጉ ተገልጿል።












