የኬንያ መንግሥት ባየር ሙኒክና ኤፍሲ አያክስ እ.አ.አ በጥር 5፣ 2027 የሚያደርጉትን ጨዋታ ተከትሎ የማንቸስተር ዩናይትድና የአርሰናል የወዳጅነት ጨዋታን በራይላ ኦዲንጋ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ለማስተናገድ እያጠና መሆኑ ተጠቆመ።
የኬንያ የውስጥ ጉዳይ ካቢኔ ጸሐፊ ኪፕቹምባ ሙርኮመን በዛሬው እለት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ተቀናቃኞቹ ማንቸስተር ዩናይትድና አርሰናል ለወዳጅነት ጨዋታ ወደ ኬንያ ሊመጡ እንደሚችሉ ፍንጭ ሰጥተዋል። ጨዋታው ኬንያ፣ ኡጋንዳና ታንዛኒያ በጋራ ከሚያዘጋጁት የአፍሪካ ዋንጫ (AFCON) በፊት፣ ከሰኔ እስከ ሐምሌ ባለው ጊዜ እንደሚካሄድ ይጠበቃል።
ሙርኮመን በቀጣዩ ዓመት ሐምሌ ወር ማንቸስተር ዩናይትድና አርሰናል በናይሮቢ እንዲጫወቱ ለማድረግ መንግሥት ሁኔታዎችን እያጠና እንደሆነ አመልክተዋል።
ጨዋታው 60 ሺህ ተመልካች የመያዝ አቅም ባለው ራይላ ኦዲንጋ ስታዲየም የሚካሄድ ሲሆን፣ የመግቢያ ትኬት ዋጋው 2,500 የኬንያ ሺሊንግ እንደሚሆን ተገልጿል።
ሙርኮመን ጨዋታው ዓለም አቀፍ ትኩረት እንደሳበና ውድድሩን ለመመልከት ደጋፊዎች ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ወደ ኬንያ እንደሚመጡ ተናግረዋል።
“ጨዋታውን ለመታደም 5,000 አውሮፓውያን ወደ ኬንያ ይመጣሉ። ከግብፅና ከናይጄሪያም የሚመጡ ደጋፊዎች አሉ” ሲሉ ሙርኮመን አክለዋል።
በተያያዘ ዜና፣ ባየር ሙኒክና አያክስ የሚያደርጉት ጨዋታ 60 ሺህ ተመልካች የመያዝ አቅም ያለውንና ግንባታው ወደ ማጠናቀቂያው የተቃረበውን ስታዲየም በይፋ ያስመርቃል።
ሁለቱም ክለቦች በጨዋታው የሚችሉትን እጅግ ጠንካራ ቋሚ ተሰላፊዎቻቸውን ለማሰለፍ ቃል እንደገቡ ተዘግቧል። ይህም ጨዋታው የቀድሞ ታዋቂ ተጫዋቾችን ወይም የአካዳሚ ተጫዋቾችን ያካተተ የማሳያ ጨዋታ እንደማይሆን ያመለክታል።
ከእግር ኳስ ጨዋታው በተጨማሪ፣ አዘጋጆቹ የ12 ሰዓት የደጋፊዎች ፌስቲቫል ለማዘጋጀት እየሠሩ ነው። በፌስቲቫሉም ዓለም አቀፍ የሙዚቃ ትርዒቶች፣ የልዩ እንግዶች አቀባበልና አገልግሎቶች፣ እንዲሁም የኬንያን ባህልና የስፖርት ተሰጥኦ የሚያስተዋውቁ ተግባራት ይካተታሉ።
የባየር ሙኒክና የአያክስ ጨዋታ መረጋገጡ ከመገለጹ በፊትም ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ማንቸስተር ዩናይትድንና አርሰናልን ለወዳጅነት ጨዋታ ወደ ስታዲየሙ ለማምጣት ዕቅድ እንዳለ ፍንጭ ሰጥተው ነበር።
የፕሬዚዳንቱ ቀደምት አስተያየት በኬንያ የእግር ኳስ ደጋፊዎች ዘንድ የታቀደው ጨዋታ በእርግጥ ይካሄድ ይሆን? የሚል ግምትና ውይይት አስነስቶ ነበር።
ይሁን እንጂ ሙርኮመን በቅርቡ የሰጡት መግለጫ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ከሚገኙ ታላላቅ ክለቦች ኮከብ ተጫዋቾችን በኬንያ ምድር ላይ የማየት የደጋፊዎችን ተስፋ እንደገና አነቃቅቷል።
ማንቸስተር ዩናይትድና አርሰናል በኬንያ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ደጋፊዎች ያሏቸው ክለቦች በመሆናቸው፣ በሁለቱ መካከል የሚደረግ ጨዋታ ለአገሪቱ የእግር ኳስ ወዳጆች ትልቅ መስህብ እንደሚሆን ይጠበቃል።










