ዴሞክራቶች በአሜሪካ ኮንግረስ አብላጫ ድምፅ ማግኘታቸው፣ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በውጭ ዕርዳታ ላይ የወሰዱትን የቅነሳ እርምጃ ለመቀልበስ አዲስ ፖለቲካዊ ትግል ከፍቷል። በዚህም በአፍሪካ የኤችአይቪ ሕክምና፣ የሰብዓዊ ዕርዳታና የልማት ፕሮግራሞች የወደፊት ሁኔታ በትኩረት ላይ ይገኛል።
በ2026 የአሜሪካ አጋማሽ ዘመን ምርጫ በተወካዮች ምክር ቤትና በሴኔት ቁጥጥር ያገኙት ዴሞክራቶች፣ ከጥር 2027 ጀምሮ የትራምፕን አስተዳደር በበለጠ ለመቆጣጠር፣ የመንግሥትን ወጪ ለመመርመርና የተቋረጡ የውጭ ዕርዳታ ፕሮግራሞች እንዲመለሱ ጫና ለማሳደር ዕድል ያገኛሉ። ሆኖም የትራምፕን የዕርዳታ ቅነሳ መቀልበስ ቀላል አይሆንም። ፕሬዚዳንቱ በውጭ ፖሊሲና በዓለም አቀፍ ዕርዳታ አፈጻጸም ላይ ሰፊ ሥልጣን አላቸው። ዴሞክራቶችም የበጀት ሥልጣናቸውን፣ ሕግ አውጪነትንና የቁጥጥር ሥራቸውን ተጠቅመው የአስተዳደሩን ውሳኔዎች ለመቃወም ይችላሉ።
ቅነሳው ለአፍሪካ ከልማት ባሻገር ከጤና አገልግሎቶች፣ ከምግብ ዋስትና፣ ከግጭት መከላከልና አሜሪካ በአህጉሪቱ ከሚኖራት ተጽዕኖ ጋር የተያያዘ ነው።
የአሜሪካ ዕርዳታ ቅነሳ በአፍሪካ ላይ ያስከተለው ጫና
በየካቲት 2025 የደኅንነት ጥናት ተቋም (Institute for Security Studies – ISS) ያወጣው ትንተና፣ የትራምፕ የዕርዳታ ቅነሳ በአፍሪካ ላይ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ተፅዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ገምቷል።
በተቋሙ የአፍሪካ የወደፊትና ፈጠራ ክፍል ኃላፊ ጃኪ ሲሊየርስ የተመራው ጥናት፣ የአሜሪካ ዕርዳታ መቀነስ በአንድ ዓመት ውስጥ ተጨማሪ 5.7 ሚሊዮን አፍሪካውያንን ወደ ከፍተኛ ድህነት ሊከትት እንደሚችል አመልክቷል። ጥናቱ ከሃራ በታች ያለው የአፍሪካ ኢኮኖሚ በ2030 ድጋፉ ቢቀጥ ሊኖረው ከሚችለው ጋር ሲነጻጸር በ4.6 ቢሊዮን ዶሃር ያነሰ ነው።
ሲሊየርስ፣ “የአሜሪካ ለአፍሪካ የምታደርገው ዕርዳታ በጥልቀትና በችኮላ መቀነሱ ለአሜሪካ ያለውን አመለካከት በእጅጉ ይጎዳል፤ ድህነትንም ያባብሳል” ብለዋል።
የጤና ዘርፉም በቅነሳው ከተጎዱት ዋና ዋና ዘርፎች አንዱ ነው። በአፍሪካ የኤችአይቪ መከላከል፣ ምርመራና ሕክምናን ሲደግፍ የቆየው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የኤድስ ድንገተኛ ዕርዳታ ዕቅድ (PEPFAR)፣ ዋሽንግተን የውጭ ዕርዳታ ሥርዓቷን እንደገና በማዋቀሯ መስተጓጎል ገጥሞታል።
ሆኖም የትራምፕ አስተዳደር ከአፍሪካ የጤና ድጋፉን በሙሉ አላቋረጠም። በአዲስ የሁለትዮሽ ስምምነቶች አንዳንድ አገራት የቀጠለ ወይም የጨመረ ድጋፍ ሲያገኙ፣ ሌሎች ደግሞ የዕርዳታ ቅነሳና የራሳቸውን ወጪ የመሸፈን ጫና ገጥሟቸዋል።
ለምሳሌ፣ ኬንያ ከ2026 እስከ 2030 በዓመት በግምት 320 ሚሊዮን ዶላር የአሜሪካ የጤና ድጋፍ እንደምታገኝ የኦቨርሲይዝ ልማት ተቋም (ODI) ገልጿል። ይህም ከ2024 የድጋፍ መነሻ ደረጃ በ11 በመቶ ገደማ የበለጠ ነው።
ሆኖም ስምምነቱ ኬንያ በዓመት 170 ሚሊዮን ዶላር ገደማ የራሷን የገንዘብ ድርሻ እንድታዋጣ ይጠይቃል። ይህም ናይሮቢ አስፈላጊ የጤና አገልግሎቶችን ለመደገፍ የሚኖርባትን የበጀት ጫና ይጨምራል።
ዴሞክራቶች በበጀት ላይ ያለውኝ ሥልጣናቸውን ሊጠቀሙ ይችላሉ
ዴሞክራቶች የትራምፕን የዕርዳታ ቅነሳ ለመቃወም ከሚጠቀሙባቸው ዋና መሣሪያዎች አንዱ የኮንግረስ የበጀት ሥልጣን ነው።
በአሜሪካ ሕገ መንግሥት አንቀጽ አንድ መሠረት፣ የመንግሥትን ወጪ የመወሰን ሥልጣን የኮንግረስ ነው። እንዲሁም በ1974 የወጣው የገንዘብ መከልከል ቁጥጥር ሕግ (Impoundment Control Act)፣ ፕሬዚዳንቱ የኮንግረስን ፈቃድ ሳያገኙ የተፈቀደን በጀት እንዳያግዱ ይገድባል።
ይህም ዴሞክራቶች የኤችአይቪ ሕክምናን፣ የሰብዓዊ ዕርዳታንና የልማት ፕሮግራሞችን ለመጠበቅ በበጀት ሕጎች ላይ ተፅዕኖ እንዲያሳድሩ ያስችላቸዋል። የUSAID መልሶ ማዋቀርን መመርመርና የተቋረጡ ውሎችን በተመለከተ ባለሥልጣናትን መጠየቅም ይችላሉ።
ሆኖም የኮንግረስ ቁጥጥር የውጭ ፖሊሲን በሙሉ የመወሰን ሥልጣን አይሰጣቸውም። ትራምፕ በኮንግረስ የሚወጣን ሕግ የመቃወም ሥልጣን አላቸው። የፕሬዚዳንቱን ቬቶ ለመሻር ደግሞ በሁለቱም ምክር ቤቶች የሁለት ሦስተኛ ድጋፍ ያስፈልጋል።
በመሆኑም ዴሞክራቶች የተቋረጡ ድጋፎችን በሙሉ ወዲያውኑ ከመመለስ ይልቅ፣ በበጀትና በፕሮግራሞች አፈጻጸም ላይ የረዥም ጊዜ ትግል ሊያደርጉ ይችላሉ።

የዕርዳታ ቅነሳው የአሜሪካን ተፅዕኖ ሊያዳክም ይችላል
የአሜሪካ ዕርዳታ መቀነስ በአፍሪካ የደኅንነት ሁኔታና በዓለም አቀፍ ተፅዕኖዋ ላይም ውጤት ሊኖረው ይችላል።
ግንቦት 14 ቀን 2026 በሳይንስ መጽሔት የታተመ ጥናት፣ ከዚህ ቀደም ከፍተኛ የአሜሪካ ዕርዳታ ሲያገኙ በነበሩ አካባቢዎች የUSAID ሥራ ከተቋረጠ በኋላ የትጥቅ ግጭቶች፣ ሰልፎችና አመፆች መጨመራቸውን አሳይቷል።
ተመራማሪዎቹ የልማት ዕርዳታ ተጋላጭ ማኅበረሰቦች ባሉባቸው አካባቢዎች የኢኮኖሚና ማኅበራዊ መረጋጋትን ለመጠበቅ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
በሌላ በኩል አሜሪካ የልማት ተሳትፎዋን ስትቀንስ፣ ቻይናና ሌሎች ዓለም አቀፍ አጋሮች በአፍሪካ የኢኮኖሚ፣ የመሠረተ ልማትና የዲፕሎማሲ ግንኙነቶቻቸውን ለማጠናከር ዕድል ሊያገኙ ይችላሉ።
ይሁን እንጅ የአሜሪካ ድጋፍ መቀነስ በቀጥታ ለቻይና ጥቅም ያስገኛል ማለት አይደለም። የአፍሪካ መንግሥታትም የራሳቸውን የገንዘብ ምንጮች ለማሳደግና አማራጭ የዓለም አቀፍ አጋርነቶችን ለመፍጠር እየሠሩ ነው።
አፍሪካ ከዕርዳታ በላይ ትፈልጋለች
የአሜሪካ ዕርዳታ መቋረጥ አፍሪካ በውጭ ለጋሾች ላይ ያላትን ጥገኝነት እንዴት መቀነስ እንደምትችል የሚደረገውን ክርክር አጠናክሮታል።
በጥር 2026 የታተመው የODI ትንተና፣ ኢትዮጵያን፣ ናይጄሪያንና ጋናን ጨምሮ አንዳንድ አገራት የአሜሪካ ድጋፍ መስተጓጎልን ተከትሎ የሀገር ውስጥ በጀታቸውን ለማሳደግና አማራጭ የገንዘብ ምንጮችን ለመፈለግ እየሠሩ መሆኑን ዘርዝሯል።
የናይጄሪያ የጤና ሚኒስትር መሐመድ አሊ ፓቴ፣ “ጤናማ ማኅበረሰብን በሌሎች አገራት ልግስና ላይ ብቻ ተመርኩዘን መገንባት አንችልም” ብለዋል።
ይህም አፍሪካውያን መንግሥታት በልማት ፕሮግራሞች ላይ የበለጠ ባለቤትነት እንዲኖራቸውና በውጭ ዕርዳታ ላይ ያላቸውን ጥገኝነት እንዲቀንሱ ያለውን ፍላጎት ያሳያል።
ለዴሞክራቶችም የቀድሞውን የዕርዳታ ሥርዓት በቀጥታ መመለስ ብቻ በቂ አይሆንም። የዕርዳታ ጥገኝነትን፣ ተጠያቂነትንና የአፍሪካ አገራትን ባለቤትነት የሚያጠናክር አሠራር መፍጠርም ያስፈልጋል።
የ2027 ትልቁ ፈተና
አዲሱ ኮንግረስ በ2027 የፌዴራል በጀት ሲወስን፣ ዴሞክራቶች የትራምፕን የውጭ ዕርዳታ ፖሊሲ ለመቃወምና የተቋረጡ ድጋፎችን ለመመለስ ዕድል ያገኛሉ።
ሆኖም የውጭ ዕርዳታን ከሀገር ውስጥ የወጪ ፍላጎቶች ጋር ማመጣጠንና ከፕሬዚዳንቱ ቬቶ ሊተርፍ የሚችል ሕግ ማጽደቅ ፈተና ይሆንባቸዋል። ለአፍሪካ አገራት ግን አስቸኳይ ጉዳዩ የጤና፣ የሰብዓዊ ዕርዳታና የልማት ፕሮግራሞች በቂ የገንዘብ ድጋፍ ማግኘታቸውን መቀጠላቸው ነው።
ትራምፕ የአሜሪካን ዕርዳታ ወደ ሁለትዮሽ ስምምነቶች፣ የሀገር ውስጥ የገንዘብ ተሳትፎና በግልጽ በተቀመጡ የአሜሪካ ጥቅሞች ላይ እንዲያተኩር አድርገዋል። ዴሞክራቶች ይህን አካሄድ ሊቃወሙ ቢችሉም የፕሬዚዳንቱን የውጭ ፖሊሲ በሙሉ መቀየር አይችሉም።
ዴሞክራቶች የትራምፕን የዕርዳታ ፖሊሲ ለመቆጣጠርና አቅጣጫውን ለመቀየር የኮንግረስ ሥልጣን አግኝተዋል። ይህንን ሥልጣን ተጠቅመው የተቋረጡ ድጋፎችን መመለስ ይችላሉ ወይ? የሚለው ጥያቄ የ2027 የኮንግረስ አብላጫ ድምፃቸውን የሚፈትነው ዋነኛው ጉዳይ ይህ ይሆናል።









