በቦይንግ እና ሎክሂድ ማርቲን የጋራ ባለቤትነት ሥር የሚገኘው ዩናይትድ ላውንች አላያንስ (ULA) የተባለ ኩባንያ የሚያስተዳድረው ቩልካን ሮኬት እሁድ ዕለት በበረራ ላይ ከሽፎ ለአማዞን የሌኦ የኢንተርኔት አገልግሎት የታቀዱ 40 ሳተላይቶችን ማውደሙን ሮይተርስ ዘግቧል።
ሮኬቱ በፍሎሪዳ ከሚገኘው ኬፕ ካናቬራል የጠፈር ኃይል ጣቢያ ከተነሳ ከ10 ደቂቃ ገደማ በኋላ ችግር አጋጥሞት ሳተላይቶቹን ወደ ምህዋር ማስገባት ሳይችል ቀርቷል።
የችግሩ መንስኤ ወዲያውኑ አለመታወቁንና ULA ምርመራ ማካሄድ እንደሚፈልግ ዘገባው ጠቅሷል።
ክስተቱ ኩባንያው እ.ኤ.አ. በ2006 ከተቋቋመ ወዲህ የመጀመሪያው ያልተሳካ የሮኬት ተልዕኮ ሆኗል። ውድቀቱ ረጅም የቴክኒክ ምርመራ እንዲካሄድ ሊያደርግ ስለሚችል፣ ቩልካን ሮኬት ለበርካታ ወራት ከበረራ ውጭ ሊሆን ይችላል። ይህም በአሜሪካ የሮኬት ማስወንጨፍ ዘርፍ ያለውን ጫና ሊያባብስ ይችላል ተብሏል።
የእሁዱ ተልዕኮ ቩልካን ሮኬት እ.ኤ.አ. በ2024 የመጀመሪያ በረራውን ካደረገ ወዲህ አምስተኛው ሲሆን፣ በዘጠኝ ወራት ውስጥ የመጀመሪያው በረራ ነበር። ቀደም ባሉት በረራዎች የሮኬቱ ጠንካራ ነዳጅ ማቀጣጠያ ክፍሎችና በአማዞን መሥራች ጄፍ ቤዞስ በተመሠረተው ብሉ ኦሪጂን የሚቀርቡት የBE-4 ሞተሮች ላይ የቴክኒክ ችግሮች ተስተውለው ነበር።
ውድቀቱ አማዞን ከ11 ሺህ በላይ ሳተላይቶችና በዓለም ዙሪያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ደንበኞች ያሉትን የስፔስኤክስ ስታርሊንክ የሳተላይት ኢንተርኔት አገልግሎትን ለመወዳደር የሚያደርገውን ክስተት ፈተና ውስጥ ከቶታል።
አማዞን እ.አ.አ ከ2025 ጀምሮ በ14 የሮኬት ማስወንጨፍ ተልዕኮዎች 398 የሌኦ ሳተላይቶችን ወደ ምህዋር ማስገባት ችሏል። ይህም ዓለም አቀፍ የኢንተርኔት ሽፋን ለማቅረብ ከያዘው 3,236 ሳተላይቶች ዕቅድ 12 በመቶ ገደማ ነው። ኩባንያው በዚህ ዓመት የመጀመሪያ የኢንተርኔት አገልግሎቱን ለመጀመር አቅዶ ነበር።
አማዞን ULA ከዚህ ክስተት ትምህርት በመውሰድ የቩልካን ሮኬትን የረጅም ጊዜ ዕቅድ እንደሚያሳካ እምነት እንዳለው ገልጿል።













