ማዳጋስካር በታሪኳ ከፍተኛ ነው የተባለለትን የደረጃ 4 አውሎ ንፋስ (Cyclone Gezani) አስተናግዳለች። በሰዓት 210 ኪሎ ሜትር የሚጓዘው ይህ ኃይለኛ ንፋስ በተለይም የሀገሪቱን ሰሜን ምስራቅ የባህር ዳርቻዎች ክፉኛ መትቷል።
አውሎ ንፋሱ መሬት የነካው የዓለም የቫኒላ ምርት ማዕከል በሆነችው አንታላሃ (Antalaha) ከተማ አቅራቢያ ነው።
የሀገሪቱ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ቢሮ (BNGRC) እንዳስታወቀው ከ45,000 በላይ ሰዎች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው በትምህርት ቤቶችና በመንግስት መጠለያዎች ውስጥ ይገኛሉ።
እስካሁን የ14 ሰዎች ህይወት ማለፉ የተረጋገጠ ሲሆን የመገናኛ መስመሮች በተቆረጡባቸው ገጠራማ አካባቢዎች ቁጥሩ ሊጨምር እንደሚችል ተሰግቷል።
ማዳጋስካር ለዓለም ገበያ ከምታቀርበው የቫኒላ ምርት ውስጥ 40 በመቶው መውደሙ ተገልጿል። ይህም በዓለም አቀፍ የቫኒላ ዋጋ ላይ ከፍተኛ መናር ሊያስከትል እንደሚችል ባለሙያዎች ይተነብያሉ።












