Loading...

በዳቮስ በተካሄደው የአለም የኢኮኖሚ ጉባኤ ላይ የተነሱ ዋናዋና ጉዳዮች ምንድን ናቸው?

ከ130 ሀገራትና ቀጣናዎች የተውጣጡ 3000 ተሳታፊዎች የተገኙበት በስዊዘርላንድ ዳቮስ ሲካሄድ የነበረው የአለም የኢኮኖሚ ጉባኤ በትናንትናው እለት ተጠናቋል። በዚህ ጉባኤ ላይ ዋና አደንዳ የነበሩትን የአሜሪካውን ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕን ጨምሮ የ65 ሀገራት መሪዎችና የኩባንያ ስራ አስፈጻሚዎችን ለቀናት መክረዋል።

በጉባኤው ላይ የተነሱት ዋናዋና ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው።

ታሪፍ

ትራምፕ ግሪንላንድን የመጠቅለል ህልማቸውን በተቃወሙት የአውሮፖ አጋሮቻቸው ላይ ታሪፍ እንደሚጥሉ ማስፈራራታቸው መነጋገሪያ ከሆኑ አጀንዳዎች መካከል ቀዳሚው ነበር። ይህ አውሮፓ ከዚህ በኋላ በአሜሪካ መተማመን አትችልም የሚለውን የአንዳንድ ኩባንያዎች ስራ አስፈጻሚዎችን  ስጋት ያጠናከረ ነበር።

“ዛሬ ላይ የኩባንያ ስራ አስፈጻሚዎችን ብትጠይቋቸው፣ ምን ይፈልጋሉ? መረጋጋት፣ ተተንባይነትና የህግ የበላይነት” ሲሉ የካናዳ የፋይናንስ ሚኒስትር መናገራቸውን ሮይተርስ ነው የዘገበው። የትራምፕ አያያዝ የንግድ አማራጮችን ከአሜሪካ ተጽኦኖ ነጻ ለማድረግና እርስበርስ የንግድ ልውውጥ ለማድረግ እየሰሩ ያሉ ሀገራትን የበለጠ የሚገፋፋ ሆኗል።  የፋይናንስ አገልግሎት ተቋማት በዚህ አመት የተሻለ የፋይናንስ እንቅስቃሴ እንደሚያሳዩ ተስፋ ቢያደርጉም፣ የአሜሪካ ፖሊሲ፣ ጂኦፖለቲካዊ ሁነቶች፣ አርቴፊሻል ኢንተሊጀንስና የፋይናንስ ቴክኖሎጂዎች መናጋት ሊፈጥሩ ይችላሉ የሚል ስጋት አላቸው።

ጂኦፖለቲካዊ ጉዳዮች

የአውሮፓ መሪዎች ከትራምፕ ጋር መጋፈጥ ያለውን ዋጋ ተገንዝበዋል። የትራምፕ በዴንማርክ ስር የምትተዳደረውን አብዛኛው ክፍሏ በረዶ የሆነችውን ግሪንላድን ለመጠቅለል ማቀዳቸው የአውሮፓውያንን የግዛት ሉአላዊነት  መርህ ጥሷል።
በዚህ ምክንያት አውሮፓውያን ከሚተማመኑባት አሜሪካ ጋር ያላቸው የትራንስአትላንቲክ ግንኙነት ፈተና ላይ የወደቀ ሲሆን በርካታ የአውሮፓ መሪዎችና ስራ አስፈጻሚዎች የትራምፕ አስተዳደርን አዝማሚያ ደስ የማይል ሆኖ አግኝተውታል።

ትራምፕ ግሪንላንድን በተመለከተ ከአውሮፓ ጋር ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ከገለጹ በኋላ የታክስ ማስፈራሪያቸውንም ለጊዜውም ቢሆን ትተውታል። ይህን ተከትሎ ትራምፕ በተለይም ወደ ዋይትሀውስ ከገቡ ጀምሮ እንደሚፈቱት ሲገልጹ የነበረው የዩክሬን-ሩሲያ ጦርነት ውይይት ተደርጎበታል። የአሜሪካ፣ የሩሲያና የዩክሬን ባለስልጣናት የሰላም ንግግሩ መሻሻሎች ማሳየቱን ቢገልጹም፣ የሰላም ስምምነት እስካሁን የማይጨበጥ ሆኗል።

አርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ

የቴስላና ንቫዲያ ስራ አስፈጻሚዎችን ጨምሮ የበርካታ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ስራ አስፈጻሚዎች በዳቮስ በሙሉ አቅማቸው ተሳትፈዋል። ስራ አስፈጻሚዎች እንደሚሉት ከሆነ በዚህ አመት የሚኖረው የአርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ(ኤአይ) ኩባንያዎች ገበያ ከ2025 መጨረሻ ከነበረው ከፍ ይላል።

የስራ እድሎች ቢጠፉም፣ አዳዲሶች ይፈጠራሉ ሲሉ ስራ አስፈጻሚዎቹ የኤአይን አስፈላጊነት ተከላክለዋል። ኤአይ ሰራተኞችን ለመቀነስ እንደምክንያት ቢቀርብም፣ መንስኤ ሊሆን እንደማይችል ሮይተርስ ያናገራቸው ሁለት የንግድ መሪዎች ተናግረዋል። የማህበራት ስራ አስኪያጆች ግን ኤአይ የስራ እድልን በማጥፋት የኢኮኖሚ ልዩነት የበለጠ እንዲሰፋ ያደርጋል የሚል ስጋት አንጸባርቀዋል።

መከላከያ

ፕሬዝደንት ትራምፕ ግሪንላንድን በኃል እንደማይዙ ይፋ ካደረጉ በኋላ አለም ትንሽ ተንፈስ ብሏል። ነገርግን ጥቂት ስራ አስፈጻሚዎች እየጨመረ ባለው የአውሮፓና የአሜሪካ የመከላከያ በጀት ላይ በፕሮጀክቶች ግንባታና በቅጥር ጨምሮ በተለያዩ ስራዎች እንሳተፋለን የሚል ተስፋ ስንቀዋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ የቬኔዙዌላውን ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮን ለመያዝ ጥቅም ላይ ስለዋለው ሶኒክ ስለተባለው ሚስጥራዊ መሳሪያም ተናግረዋል። ሩሲና ቻይና ወደ ኃላ ሄደው መጀመር ይኖርባቸዋል ሲሉ ተደምጠዋል። ክሬሚሊን በበኩሉ የሩሲያ ሰክሬት ሰርቪስ ጉዳዩን እየመረመረው እንደሆነ ገልጿል።

Share this article

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው