የኤርትራ መንግሥት፣ ኢትዮጵያ በአስመራ የሚገኘውን ኤምባሲዋን ከዘጋች እና በአዲስ አበባ የሚገኙ 10 የኤርትራ ዲፕሎማቶችን ሀገር ለቀው አእንዲወጥ ካወጀች በኋላ፣ በምላሹ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሁሉንም የዲፕሎማሲ ግንኙነት ማቋረጧን አስታውቋል።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ቀደም ብሎ በአስመራ የሚገኘውን ኤምባሲ ለመዝጋት መወሰኑን ያስታወቀ ሲሆን፣ ይህንንም ኤርትራ በኢትዮጵያ ላይ እያደረገች ባለችው ተደጋጋሚ ቀጥተኛ ጥቃትና ጠበኛ እርምጃ ምክንያት መሆኑን ገልጿል። ሚኒስቴሩ በአዲስ አበባ የሚገኙ 10 የኤርትራ ዲፕሎማቶች ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ደህንነት “ቀጥተኛ ስጋት በሚያስከትሉ” እንቅስቃሴዎች ላይ በመሳተፋቸውና የቪየና ስምምነቶችን በመጣሳቸው በ48 ሰዓታት ውስጥ ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ አዟል።
የኤርትራ የኢንፎርሜሽን ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል በኤክስ ላይ እንደገለጹት ኢትዮጵያ ላለፉት ሶስት አመታት በኤርትራ ላይ “ያልተቋረጠ የጠላትነት አጀንዳ እያራመደች” ነው፤ ይህም “የጦርነት አዋጅ” ተደርጎ የሚወሰድ መሆኑን ገልጸዋል።
“በእነዚህ ፈታኝ ጊዜያት ኤርትራ አደገኛ መባባስን ለመከላከል በማሰብ ትዕግሥትና ራስን የመግዛት ባህሪይ አሳይታለች” ሲሉ አክለዋል።
የማነ የኢትዮጵያን እርምጃ በተመለከተ ሲናግሩ ኤርትራ “በተመሳሳይ መልኩ ምላሽ ከመስጠትና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሁሉንም የዲፕሎማሲ ግንኙነት ከማቋረጥ” ውጭ ምንም አማራጭ እንዳልቀረላት ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ እርምጃ በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግም ግጭት መከሰቱን ተከትሎ የመጣ ነው። በተጨማሪም ኢትዮጵያ ጎረቤት አገራቷ ሱዳንና ኤርትራ በአገሪቱ ውስጥ ለሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ቡድኖች የገንዘብ ድጋፍ እያደረጉ ነው ስትል በከሰሰችበት ወቅት የተወሰደ እርምጃ ነው። ሆኖም ሁለቱም አገራት ክሱን በተደጋጋሚ አስተባብለዋል።












