Loading...

ትራምፕ የሁለት ሳምንት ተኩስ አቁም ካሳወቁ በኋላ የአለም የነዳጅ ዋጋ ከ100 ዶላር በታች ዝቅ አለ

የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር ለሁለት ሳምንት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ካሳወቁ በኋላ የአለም የነዳጅ ዋጋ በበርሜል ከ100 ዶላር በታች ወርዷል።

ትራምፕ በኢራን ላይ ሊወስዱት የነበረውን ከባድ ጥቃት ለማቆም የተስማሙት፣ ኢራን ዘግታው የነበረውን የአለም 20 በመቶ የነዳጅ ፍጆታ የሚተላለፍበትን የሆርሙዝ ሰርጥ ለመክፍት በመስማማቷ መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል።

ፓኪስታን፣ ትራምፕ የኢራንን ስልጣኔ ያወድማል ያሉትን ከባድ ጥቃት ሊፈጽሙ ያስቀመጡት የሰአት ገደብ ሊጠናቀቅ ጥቂት ሲቀሩት ዋሽንግተንንና ቴህራንን በማግባባት የተኩስ አቁም ስምምነቱ እንዲደረስ አድርጋለች።

ትራምፕ “ከኢራን ባለ 10 ነጥብ ሀሳብ ተቀብለናል፤ ይህ ለዘላቂ ለስምምነት መሰረት ይሆናል ብለን እናምናለን” ብለዋል።

ትራምፕ አክለውም አሜሪካና ኢራን በአብዛኞቹ አከራካሪ ጉዳዮች ላይ መስማማታቸውንና ተኩስ አቁሙ ተግባራዊ በሚሆንባቸው ሁለቱ ሳምንታት ውስጥ ለማጠናቀቅ እንደሚቻል ገልጸዋል።

“ብሬንት ፉቸርስ” በ16 ዶላር ወይም በ14.9 በመቶ ቀንሶ በበርሜል 92 ዶላር ሲሸጥ “ደብሊውቲአይ ስሊድ” (WTI Slid) በ18 ዶላር ወይም በ16.1 በመቶ ቀንሶ በበርሜል 94.79 ዶላር እየተሸጠ መሆኑን ዘገባው ጠቅሷል።

ኢራንም አሜሪካ ጥቃቷን የምታቆም ከሆነ በሆርሙዝ ሰርጥ ደህንነቱ የተጠበቀ እንቅስቃሴ እንዲኖር እንደምታደርግ ሮይተርስ የኢራኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርን አባስ አራግቺን ጠቅሶ ዘግቧል።

አሁን የታየው የነዳጅ ዋጋ ቅናሽ የሚወሰነው በተኩስ አቁሙ ተግባራዊነትና ዘላቂነት ላይ  ነው

የአሜሪካና እስራኤል ጦርነት የነዳጅ ዋጋ ባለፈው መጋቢት ወር በታሪክ ከ50 በመቶ በላይ እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል።

እስራኤልና አሜሪካ በኢራን ላይ መጠነሰፊ ዘመቻ ያካሄዱ ሲሆን ኢራንም በአጸፋ በእስራኤልና የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች በሚገኙባቸው የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ላይ የሚሳይልና የድሮን ጥቃት በመሰንዘር ጦርነቱ ጠፊ ቀጠና እንዲሸፍን አድርጋዋለች

Share this article

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው