በመካከለኛው ምስራቅ እየተባባሰ የመጣው ግጭት ዓለም አቀፉን የነዳጅ መስመር ስጋት ላይ ጥሎታል። በተለይም ኢራን የሆርሙዝ ስምጥን (Strait of Hormuz) ለመዝጋት መወሰኗ የዓለም የነዳጅ አቅርቦት 20 በመቶ በሚያልፍበት በዚህ ቀጠና ላይ ጥገኝነት ላላቸው የአፍሪካ ሀገራት አስደንጋጭ ዜና ሆኗል።
የሆርሙዝ ስምጥ (Strait of Hormuz) ምንድን ነው? ለምንስ ወሳኝ ሆነ?
የሆርሙዝ ስምጥ በዓለም ላይ ካሉ እጅግ ስልታዊ እና ስሜታዊ የባህር መስመሮች መካከል ቀዳሚው ነው። ይህ ጠባብ የባህር መተላለፊያ በሰሜን በኩል ኢራንን፣ በደቡብ በኩል ደግሞ ኦማንን እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስን ያዋስናል።
ለምን የአለም የኢኮኖሚ የልብ ትርታ ተባለ?
በዓለም ላይ በባህር ከሚጓጓዘው አጠቃላይ የነዳጅ ምርት ውስጥ 20 በመቶ (1/5ኛ) የሚሆነው በዚህ ስምጥ በኩል ያልፋል። ከሳዑዲ አረቢያ፣ ከኢራቅ፣ ከኩዌት፣ ከኳታር እና ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የሚላክ ነዳጅ ለዓለም ገበያ የሚቀርበው በዚህ ጠባብ መስመር ነው።
በዓለም ላይ በፈሳሽ መልክ የሚላከው የተፈጥሮ ጋዝ (LNG) ሲሶው (1/3ኛ) የሚጓጓዘው በዚህ መስመር ነው።
ስምጡ በጠባብነቱ (በጣም ጠባብ በሆነው ቦታው 33 ኪሎ ሜትር ብቻ ነው) በቀላሉ ለመዝጋት ወይም ጥቃት ለመፈጸም አመቺ በመሆኑ፣ በመካከለኛው ምስራቅ ለሚነሱ ግጭቶች እንደ ዋነኛ የፖለቲካ መጫወቻ ካርታ ያገለግላል።
የኒውዮርክ ሲቲ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ዳቪድ ሞንዳ (Prof. David Monda) ለሲጂቲኤን በሰጡት ቃለ ምልልስ ይህ እገዳ በአፍሪካ ላይ የሚያሳድረውን ከፍተኛ ጫና በዝርዝር ተንትነዋል።

ረጅም የነዳጅ እጥረት እና የዋጋ ንረት
አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት የራሳቸው የነዳጅ ማጣሪያ ስለሌላቸው ከባህረ ሰላጤው ሀገራት የሚመጣውን የተጣራ ነዳጅ ይጠብቃሉ። ፕሮፌሰር ሞንዳ እንዳሉት የሆርሙዝ ስምጥ መዘጋት ማለት ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ረጅም እና ውድ የሆነውን የደቡብ አፍሪካ “ኬፕ ኦፍ ጉድ ሆፕ” (Cape of Good Hope) መስመር እንዲጠቀሙ ያስገድዳቸዋል። ይህ ደግሞ፦
- የትራንስፖርት ወጪን በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል።
- የነዳጅ አቅርቦት ለሳምንታት እንዲዘገይ ያደርጋል።
- በአፍሪካ ገበያ ላይ የነዳጅ ዋጋ እንዲንር በማድረግ የኑሮ ውድነቱን ያባብሰዋል።
ነዳጅ ለትራንስፖርት ብቻ ሳይሆን ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች እና ለፋብሪካዎች ወሳኝ ነው። እንደ ናይጄሪያ እና ደቡብ አፍሪካ ያሉ ግዙፍ ኢኮኖሚዎች እንዲሁም እንደ ኢትዮጵያ እና ኬንያ ያሉ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት የነዳጅ እጥረት ካጋጠማቸው ምርታማነታቸው በከፍተኛ ሁኔታ ይወድቃል። ፕሮፌሰር ሞንዳ “አፍሪካ ለዚህ ድንገተኛ አደጋ ዝግጁ የሆነችበት መጠባበቂያ የነዳጅ ክምችት የላትም” ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።
የምግብ ዋስትና ስጋት
የነዳጅ ዋጋ መጨመር በቀጥታ ከምግብ ዋጋ ጋር የተያያዘ ነው። ምርቶችን ከገጠር ወደ ከተማ ለማጓጓዝ የሚያስፈልገው የነዳጅ ወጪ ሲጨምር ቀድሞውንም በዋጋ ንረት እየተፈተነ ያለው የአፍሪካ ህዝብ ለከፋ የምግብ እጥረት ሊጋለጥ ይችላል።
ጂኦፖለቲካዊ ጫና
ፕሮፌሰር ሞንዳ እንደሚሉት ይህ ቀውስ አፍሪካን በሁለት ጎራዎች መካከል። በአንድ በኩል ከምዕራባውያን (አሜሪካ) ጋር ያላትን ግንኙነት በሌላ በኩል ደግሞ ከኢራን እና ከአጋሮቿ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ሚዛን እንድትፈትሽ ያስገድዳታል።












