ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ድርጅት (ICRC) በሰሜን ኢትዮጵያ በድጋሚ ባገረሸው ግጭት ምክንያት ከትግራይ ክልል መውጣት አቅቷቸው የነበሩ 161 ሰዎችን “በሚመለከታቸው ሁሉም አካላት ጥያቄና ፈቃድ” ገለልተኛ አገናኝ በመሆን ማውጣት መቻሉን አስታውቋል።
ድርጅቱ ስላወጣቸው ሰዎች ማንነት በግልጽ ባይጠቅስም እንዲወጡ የተደረጉት ሰዎች በትግራይ ክልል በሚገኙ የፌዴራል መንግሥት ተቋማት ውስጥ ሲሠሩ የነበሩ የሲቪልና የጸጥታ ሠራተኞች ናቸው ተብሏል።
የትግራይ ክልልን በሚያስተዳድረው ህወሓትና በፌዴራል መንግሥት መካከል የነበረው አለመግባባት ወደ ይፋዊ ግጭት ያመራው ባለፈው ሳምንት ነበር። ቀደም ሲል ህወሓት በፌዴራል መንግሥት እውቅና የተሰጠውን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በማፍረስና በጥቅምት 2013 ዓ.ም. የተቀሰቀሰውንና ለሁለት ዓመት የቆየውን ደም አፋሳሽ ጦርነት ያስቆመውን የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ውድቅ በማድረግ ውጥረቱን ከፍተኛ ደረጃ ላይ አድርሶት ነበር።
ህወሓት በፌዴራል መንግሥት ጥቃት እንደተከፈተበት ገልጾ ራስን ወደ መከላከል ግጭት መግባቱን ካወጀ በኋላ የኢትዮጵያ አየር መንገድም በትግራይ ክልል ወደሚገኙት የመቀሌ፣ የሽረና የአክሱም አውሮፕላን ማረፊያዎች በረራ ማቆሙን ይፋ ማድረጉ የግጭቱን መክረር ያሳየ ነበር። ከቀናት በኋላ የፌዴራል መንግሥትም ከህወሓት የተቃጣበትን ጥቃት መመከቱንና ጉዳት ማድረሱን በመግለጽ፣ የግጭቱን መቀስቀስ አረጋግጧል።










