በትናንትናው ዕለት በፍላይዱባይ (flydubai) በረራ ላይ የነበሩ ተሳፋሪዎችና የበረራ ሠራተኞች፣ የረዳት አብራሪውን አውሮፕላኑን ለመከስከስ ያደረገውን ሙከራ በማክሸፍ በሳዑዲ አረቢያ ማሳረፍ መቻላቸውን የእስራኤል ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
ረዳት አብራሪው ዋና አብራሪውን በመውጋቱ፣ አውሮፕላኑ በ30 ሰከንድ ውስጥ 14 ሺህ ጫማ ያህል በፍጥነት እንዲወርድ በማድረጉ ነው ችግሩ የተፈጠረው።
ይህን ችግር የሰሙት ተሳፋሪዎችና የበረራ ሠራተኞች ፈጥነው ወደ ኮክፒት በመግባት ረዳት አብራሪውን በኃይል በመቆጣጠር፣ በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩ የፍላይዱባይ ተጠባባቂ አብራሪዎች አውሮፕላኑን በሳዑዲ አረቢያ ታቡክ እንዲያርፍ ማድረጋቸውን ባለሥልጣናቱ ገልጸዋል።
ከ10 ሰዓታት በኋላ ተሳፋሪዎቹ በሌላ የፍላይዱባይ አውሮፕላን ወደ ቴል አቪቭ ቤን ጉሪዮን አውሮፕላን ማረፊያ የደረሱ ሲሆን፣ አብዛኛዎቹ ክስተቱን አስፈሪ ሲሉ ገልጸውታል።
የእስራኤል ባለሥልጣናት እንዳሉት፣ የበረራ ቁጥር FZ1073 የሆነው ከዱባይ ወደ እስራኤል ሲበር በነበረው አውሮፕላን ላይ ረዳት አብራሪው ያደረገው ድርጊት በምርመራ ላይ ነው። እስራኤልና የአረብ ኢምሬትስ (ዩኤኢ) ግንኙነታቸውን ለማሻሻል የሚያስችለውን የአብርሃም ስምምነት እአአ በ2020 ተፈራርመዋል።
ለዓመታት በግጭት በሚታመሰው ክልል ውስጥ የተፈጠረው ይህ ክስተት የዓለምን የአቪዬሽን ደህንነት ስጋት ያጠናከረ ሲሆን፣ እስራኤል ወደ ሀገሯ በሚበሩ አብራሪዎች ላይ የምታደርገውን ቁጥጥር እንድታጠናክር አድርጓል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
ከተሳፋሪዎቹ ውስጥ አንዷ የነበረችው ሊታል ሻቻፍ፣ “ማለት የምችለው ተአምር ነበር ብቻ ነው። አስፈሪ ነገር ነበር፤ እናም እንደተረፍን ለእግዚአብሔር እናመሰግናለን። እንደምንተርፍ አስበን አልነበረም፤ አሁን ግን እግዚአብሔር ይመስገን፣ እስራኤል ደርሰናል። ወደ ቤታችን ተመልሰናል፣ ሁሉንም ሰው በማየታችንም ደስተኞች ነን” ስትል ሁኔታውን ገልጻለች።
የእስራኤል አምቡላንስ አገልግሎት አንድ የ51 ዓመት ወንድ በላይኛው የሰውነት ክፍሉ ላይ በደረሰበት ጉዳት ምክንያት ወደ ሆስፒታል መወሰዱን ገልጿል። ሰውየውም አሁን ላይ ቀላል በሚባል ሁኔታ ላይ እንዳለ ተገልጿል።

ክስተቱን “ከባድ የደህንነት ክስተት” ብለው የገለጹት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ፣ የሳዑዲ አረቢያ ባለሥልጣናት በረዳት አብራሪው ላይ ምርመራ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
ፍላይዱባይ በሰጠው መግለጫ፣ ከክስተቱ ጀርባ ያለው ምክንያት እስካሁን ያልታወቀ መሆኑን ገልጾ፣ “ያለጊዜው ግምት” እንዳይሰጥ አስጠንቅቋል። አንድ የእስራኤል ባለሥልጣን ረዳት አብራሪው የኦማን ዜጋ መሆኑን ገልጿል። ከኦማን በኩል ወዲያውኑ የተሰጠ ምላሽ አልነበረም።
የእስራኤል ባለሥልጣናት ሊከሰት የነበረውን ከባድ አደጋ አክሽፈዋል ያሏቸውን ተሳፋሪዎች አመስግነዋል። ኔታንያሁ እንዳሉት፣ በዚህ በረራ ላይ አብዛኛዎቹም የእስራኤል ዜጎች የሆኑ 174 ሰዎች ነበሩ።
የኔታንያሁ ቃል አቀባይ እንደገለጹት፣ ስሚት ማችቻር ተብሎ የተጠራው የህንድ ዜጋ የሆነው ዋና አብራሪ በደም ተሸፍኖ ወለሉ ላይ ቢወድቅም፣ የኮክፒቱን በር ለመክፈት የሚያስችለውን መክፈቻ መጫን ችሏል። ወደ ኮክፒቱ የገቡት ተሳፋሪዎች፣ ረዳት አብራሪው የአውሮፕላኑን መቆጣጠሪያ ፓነል እየመታ እንደነበር አግኝተዋል።
ከተሳፋሪዎቹ መካከል አሳፍ ራጁዋን አጥቂውን ለመያዝ ከተሳተፉት አንዱ ሲሆን፣ ግንባሩ ከትግሉ የተነሳ እየደማ እንዲህ ብሏል፦ “ይህን የምታደርገው ሳታስብ ነው፤ የልጅህን፣ የቤተሰብህን ሕይወት ለማዳን ብለህ ትሮጣለህ።”
የኔታንያሁ ጽሕፈት ቤት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቤን ጉሪዮን አየር ማረፊያ ሌላ ተሳፋሪን እያቀፉ የሚያሳይ ቪዲዮ አውጥቷል። ኔታንያሁ ከረዳት አብራሪው ጋር በነበረው ትግል ምክንያት ሸሚዙ በደም ተበክሎ የነበረውን መንገደኛ “ጀግና” ብለው አድንቀውታል።
ፍላይዱባይ በዱባይና በቴል አቪቭ መካከል በየቀኑ የመመለሻ በረራዎችን ያካሂዳል። ይህም መንገድ በእስራኤል ዜጎች በተለይ ተወዳጅ ነው። የበረራ መንገዱ በመደበኛነት በሳዑዲ አረቢያና በዮርዳኖስ የአየር ክልል ላይ ያልፋል።
በእስራኤልና በዩኤኢ መካከል የሚጓዝ የፍላይዱባይ በረራ በሳዑዲ አረቢያ ድንገተኛ ማረፊያ ሲያደርግ ይህ የመጀመሪያ ጊዜ አይደለም። እአአ በ2025 ከዱባይ ወደ ቴል አቪቭ የሚጓዝ የፍላይዱባይ በረራ በሕክምና አደጋ ምክንያት በሪያድ ማረፉን የእስራኤል ሚዲያዎች በወቅቱ ዘግበዋል።
የሳዑዲ አረቢያ ታቡክ አየር ማረፊያ ሁለቱም አብራሪዎች በደረሰባቸው ጉዳት ሆስፒታል እንደገቡ ገልጿል።
ይህ ክስተት በእስራኤል የደህንነት ስጋትን አባብሷል። የእስራኤል የደህንነት ሚ6ኒስትር ኢታማር ቤን-ግቪር፣ “ሽብርተኝነት ምንም ምህረት ሊደረግለት የማይገባው ዲያብሎስ ነው” ብለዋል።
እስራኤል ወደ እስራኤል የሚበሩ አብራሪዎችን ምርመራ ልታጠናክር ነው
የእስራኤል ሚዲያዎች ስለ ክስተቱ የሚጋጩ ሪፖርቶችን አቅርበዋል። አንዳንዶቹ ሚዲያዎች አንድ አብራሪ በራሱ ሕይወት ማጥፋት ሙከራ ለማድረግ የተሳፋሪዎችን አውሮፕላን ለማውደም እንደሞከረ ዘግበዋል። አንዳንድ የእስራኤል ሚዲያዎች መጀመሪያ ላይ አብራሪዎቹን የኦማንና የኤምሬትስ ዜጎች እንደሆኑ ሲገልጹ፣ ሌሎች ደግሞ ሩሲያዊና ዩክሬናዊ እንደሆኑ ዘግበዋል።
የኔታንያሁ ቃል አቀባይ ዶሮን ስፒልማን፣ “ወደ እስራኤል የሚበር እያንዳንዱ አብራሪ ማንነቱን እናውቃለን፣ ማን እንደሆነ እናውቃለን፣ እናም የሆነ ዓይነት የደህንነት ምርመራ እናደርጋለን” ሲሉ ለሮይተርስ ተናግረዋል።
ኔታንያሁ እሁድ ዕለት ባልተለመደ ሁኔታ በዩኤኢ ጉብኝት በማድረግ ከዩኤኢ ፕሬዚዳንት ሼክ ሞሐመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን ጋር ተገናኝተዋል። እስራኤልና ዩኤኢ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ካቋቋሙበት ጊዜ አንስቶ የቅርብ የደህንነት፣ ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶችን ገንብተዋል።
እስራኤል በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ዩኤኢን ከኢራን በተወነጨፉ ጥቃቶች ራሷን እንድትከላከል አይረንዶም (Iron Dome) የተባሉትን የአየር መከላከያ ሥርዓቶችን ሰጥታለች። እነዚህ ሥርዓቶች የተሰጡት እስራኤልና አሜሪካ በኢራን ላይ ጥቃት ከጀመሩ በኋላ ሲሆን፣ የእስራኤል ሠራተኞችም ሥርዓቶቹን ለማስኬድ በዩኤኢ ውስጥ ተሰማርተዋል። የዩኤኢ መንግሥት ስለ ፍላይዱባይ ክስተቱ እስካሁን አስተያየት አልሰጠም። ነገር ግን በዱባይ የሚገኘው ንብረትነቱ የመንግሥት የሆነው አየር መንገዱ፣ በኮክፒት ውስጥ “ግጭት” እንደተፈጠረና ከዚያም በረራው ወደ ታቡክ ተቀይሮ በደህና እንዳረፈ ገልጿል። የዩኤኢ የአቪዬሽን ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን (GCAA) ደግሞ በበረራው ላይ አጋጥሞ የነበረው የደህንነት ችግር በቁጥጥር ስር ውሏል ብሏል።












