በኡጋንዳ መዲና ካምፓላ በሚገኝ አንድ የሕፃናት ማቆያና መዋያ ማዕከል (Daycare Center) ውስጥ በደረሰ አሰቃቂ ጥቃት የአራት ሕፃናት ሕይወት ማለፉን የኡጋንዳ ፖሊስ አስታወቀ።
ጥቃቱ የደረሰው ትላንት ሐሙስ መጋቢት 24 ቀን 2018 ዓ.ም (April 2, 2026) ረፋድ 5:00 ሰዓት ገደማ በካምፓላ ማኪንድዬ ክፍለ ከተማ፣ ጋባ (Ggaba) ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው።
“ጋባ የሕፃናት እድገት ፕሮግራም” በተሰኘው የሕፃናት ማቆያ ውስጥ አንድ ግለሰብ በሕፃናቱ ላይ ጥቃት እያደረሰ መሆኑን የደረሰው ጥቆማ ተከትሎ ፖሊስ በሥፍራው ደርሷል።
በዚህ ዘግናኝ ድርጊት ሕይወታቸውን ያጡት አራቱም ሕፃናት በማዕከሉ ውስጥ የሚማሩ ሲሆኑ እድሜያቸው ከ2 እስከ 3 ዓመት የሆኑ ናቸው።
ፖሊስ ኦኬሎ ክሪስቶፈር ኦኒዩም የተባለውን የ39 ዓመት ግለሰብ በወንጀሉ ሥፍራ በቁጥጥር ሥር አውሏል። ተጠርጣሪው በአሁኑ ወቅት በፖሊስ ምርመራ እየተደረገበት ሲሆን ይህን “አስነዋሪ ድርጊት” ለመፈጸም ያነሳሳው ምክንያትና የኋላ ታሪኩ እየተጣራ መሆኑ ተገልጿል።
የኡጋንዳ ፖሊስ ለተጎጂ ቤተሰቦች ጥልቅ መጽናናትን እየተመኘ ለጉዳዩ ፍትህ እንዲሰጥ አስፈላጊው ምርመራ ሁሉ እንደሚደረግ ቃል ገብቷል።












