ለቀንድና ለስጋ አደን በሚያደርጉ ህገወጥ የእንስሳት አዳኞች (poachers) ጠፍቶ የነበረው አውራሪስ ከ40 አመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደኡጋንዳው ኪደፖ ቫሊ ብሔራዊ ፓርክ ተመልሷል።
ባለፈው ማክሰኞ ሁለት ነጭ አውራሪሶች ከግለሰብ ማቆያ(ራንች) ወጥተው ረጅም ጉዞ ካደረጉ በኋላ የመጨረሻው አውራሪስ በ1983 ከተገደለበት ፓርክ መድረሳቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ህገወጥ አዳኞች ያኔ በኡጋንዳ የነበረውን አለመረጋጋት በመጠቀም በኪደፖና በሌሎች የሀገሪቱ ፓርኮች ያሉ ሁሉንም አውራሪሶች ገድለዋል። በዚህ ምክያት እነዚህ ግዙፍ አጥቢዎች ከሀገሪቱ ሙሉ በሙሉ ጠፍተው ነበር።አሁን ላይ የኡጋንዳ የዱር እንሰሳት ባለስልጣን ጉዳዩን በበላይነት እየተከታተለው ይገኛል።
“ይህ ክስተት የአውራሪስን በድጋሚ ወደ ኪደፖ ብሔራዊ ፓርክ መመለስ ጅማሮ የሚያሳይ ነው” ሲሉ የዱር እንስሳት ባለስልጣኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ ጄምስ ሙሲንጉዚ ተናግረዋል።
ስራ አስፈጻሚው አክለውም “እነዚህን አውራሪሶች ማዛወር የፓርኩ ትልቅ ቅርስ የሆነውን ዝርያ የመመለስ የመጀመሪያው እርምጃ ነዉ” ብለዋል። ሁለቱ አውራሪሶች በግለሰብ ከሚተዳደረውና ከዋና ከተማዋ ካምፓላ 100 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ከሚገኘው ዚዋ ሪህኖ ኤንድ ዋይልድ ላይፍ ራንች በሰሜን ምስራቅ ኡጋንዳ ወደሚገኘው ሰፊ የሳቫና ሳር ወደሚኝበት ኪደፖ ፓርክ ተለቀዋል። ራንቹ ከኬንያ ጌም ሪዘርቭ አራት የደቡብ ነጭ አውራሪሶችን ካስመጣበት ከ2005 ጀምሮ ሲያረባ ቆይቷል።
ህገወጥ የእንስሳት አዳኞች በኡጋንዳ ጥብቅ የእንስሳት ፓርኮች ላይ ፈተና ሆነው የቀጠሉ ሲሆን ባለስልጣናትም ኩምቢ፣ ፓንጎሊንስና ሌሎች ሊጠፉ የተቃረቡ እንስሳትን ይዘው የተገኙ ተጠርጣሪዎችን በተደጋጋሚ ሲያስሩና ሲከሱ ይስተዋላሉ።
አውራሪስን በሚያድኑና በሚያዘዋውሩ ህገወጦች ላይ ከፍተኛ አለምአቀፍ ዘመቻ ቢከፈትም፣ ለባህላዊ መድኃኒትነት በሚሰጡት ጥቅምና በእስያ ሀገራት እንደ ጌጥ በመፈለጋቸው ምክንያት የአውራሪስ ቀንድ በገበያ ላይ ያለው ተፈላጊነት ጨምሯል።













