የዘንድሮውን የአለም ዋንጫን በሰኔ ወር እ.ኤ.አ 2026 ከሜክሲኮ እና ካናዳ ጋር ለማስተናገድ ቀጠሮ የያዘችው አሜሪካ ላይ በርካቶች ጥያቄን አስነስተዋል።
አሜሪካ የኢምግሬሽን ማመልከቻዎች እንዲቋረጡ በተለያዩ አገራት ላይ የጣለችው እገዳ የእግር ኳስ ደጋፊዎች ከሚወዱት የስፖርት ወድድር ሊያስቀራቸው እንደሚችል ስጋት የፈጠረ ጉዳይ ሆኗል።
በቅርቡ አሜሪካ 75 አገራት ላይ የጣለችው የቪዛ እግድ 15 ለአለም ዋንጫው ያለፉ አገራትን የሚነካ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ ስምንቱ የአፍሪካ አገራት ናቸው።
ከአሜሪካ በኩል የቪዛ እገዳው የሚመለከተው ለረዥም ግዜ ቆይታ የሚጓዙ ስደተኞችን እንጂ ለግዜያዊ ቆይታ የሚጓዙ ቱሪስቶችን እንዳልሆነ ቢገለጽም፥ በአለም ዙሪያ ለሚገኙ የእግር ኳስ ደጋፊዎች ሁኔታው አጠራጣሪ ሆኗል።
የኢራን እና ሃይቲ ብሄራዊ ቡድን ደጋፊዎች ካሁኑ ወደ አሜሪካ መግባት እንማይችሉ ሙሉ ለመሉ እገዳ ተጥሎባቸዋል። ሴኔጋል እና አይቮሪኮስት ደግሞ ከፊል እገዳ የተጣለባቸው አገራት ናቸው።
FIFAም በበኩሉ ቀድሞ የስታዲየም መግቢያ ትኬትን መግዛት ወደ አሜሪካ ለመግባት ዋስትና እንደማይሆን አስታውቋል።
ይህም፥ አንድ አገር የአለም አቀፍ ስፖርት ውድድር አስተናጋጅ ሆና ስትመረጥ የተሳታፊ አገራት ደጋፊዎችን የመቀበል ሃላፊትን በተመለከተ ጥያቄ ያስነሳ ሆኗል።
ጥያቄውን ካነሱ መሃል የብዙ አፍሪካ አገራትን የእግር ኳስ ቡድኖች የቀድሞ አሰልጣኝ ክላውድ ሌ ሮይ ይገኝበታል። “ከፍተኛ ቦታ ላይ የተቀመጡት የፊፋ ባለስልጣናት ከገንዘብ ይልቅ ስለኳስ ማውራት አቁመዋል” ሲል ክላውድ ሊ ሮይ ተናግሯል።
የቀድሞው የፊፋ ፕሬዝደንት ሴፕ ብላተር፥“ለደጋፊዎች አንድ ምክር ብቻ ነው ያለኝ፥ ወደ አሜሪካ እንዳትሄዱ!” የሚል መልዕክትን በX ገጻቸው ላይ አጋርተዋል።
በሌላ በኩል፥ የአሜሪካ ኢምግሬሽን ጸጥታ አስከባሪ ፖሊሶች የፈጸሟቸው ግድያዎች እና አሜሪካ አጠናክራ የቀጠለችው የኢምግሬሽን አሰሳዎች “አሜሪካ ለታዳሚዎች የደህንነት ስጋት ትሆናለች” የሚል ተቃውሞውን ያስነሱ ምክንያቶች ናቸው።












