የአለም ጤና ድርጅት(WHO) ረቡዕ እለት ባካሄደው አለም አቀፍ የጤና ጉዳዮች ኮንፍረንስ ላይ አሜሪካ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ አመጣጥ ላይ ሊኖራት የሚችልን ማንኛውንም ኢንተለጀንስ መረጃ እንድትካፈል ጥያቄ አቅርቧል። ድርጅቱ ይህን ጥያቄ ያቀረበው አሜሪካ ከድርጅቱ አባልነት እራሷን አግልላ ባለችበት ሁኔታ ውስጥ ነው።
እንደ መንግስታቱ ድርጅት የጤና ድርጅት ገለጻ ኮቪድ-19 በአለም ዙሪያ 20 ሚሊዮን ያህል ሰዎችን ገድሏል። በሰፊው እንደሚታመነው ወረርሽኙ በመጀመሪያ የታየው እ.አ.አ በ2019 መገባደጃ ላይ በቻይና ውስጥ በውሃን ከተማ ነው። ሆኖም ድርጅቱ ይህ መረጃ ሙሉ ሙሉ የተረጋጋጠ እንዳልሆነ እና የኢንተለጀንስ መረጃው አለን የሚሉ አገራት ካሉ መረጃውን እንዲያጋሩ ጠይቋል።
SARS-CoV-2 ቫይረስ ከየት እንደመጣ መረዳት ለወደፊቱ ወረርሽኞችን ለመከላከል ቁልፍ እንደሆነ ድርጅቱ የገለጸ ሲሆን አሜሪካ መረጃው ካላት እንድታጋራ ማሳሰቡ ቀድሞ በብዙሃኑ ዘንድ የበሽታው መነሻን በተመለከተ ያለውን እምነት ጥያቄ ውስጥ የከተተ ሆኗል።
እ.ኤ.አ. በጥር 2025 የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ስልጣን በመጡበት የመጀመሪያ ቀን አገራቸው ከአለም ጤና ድርጅት አባልነት መውጣቷን ይፋ ሲያደርጉ ድርጅቱን ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስርጭት ተጠያቂ አድርገው ነበር። የአሜሪካ ባለስልጣናት የጤና ድርጅቱ ተገቢውን መረጃ በአስፈላጊው ግዜ ባለመስጠቱ ለበርካታ አሜሪካውያን ሞት ሰበብ ሆኗል ሲሉ ወንጅለዋል።
የትራምፕ አስተዳደር ቫይረሱ በዉሃን ከተማ ከሚገኝ የቫይሮሎጂ ላብራቶሪ ሾልኮ ወጥቷል የሚለውን መላምት ይዟል።
የአለም ጤና ድርጅት የድርጅት በመግለጫው፥ አሜሪካ ከድርጅቱ አባልነት እራሷን ከማግለሏ በፊት ምንም አይነት የኮቪድ አመጣጥን የተመለከተ መረጃን ኣሳልፋ አልሰጠችም ብሏል።
የአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም “አንዳንድ አገራት በተለይም አሜሪካ ስለ ወረርሽኙ አመጣጥ ኢንተለጀንስ አለን ብለዋል” በማለት የአሜሪካ ባለስልጣናትን ንግግር አስታውሰዋል።
“ከወራት በፊት የተባበሩት መንግስታት የጤና ድርጅት ለአሜሪካ ባለስልጣናት ያላቸውን ማንኛውንም የኢንተለጀንስ መረጃ እንዲያካፍሉ ብንጠይቅም ምንም ምላሽ አላገኘንም” ሲሉ ረቡዕ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ዳይሬክተር ጀነራሉ ተናግረዋል።
“የተከሰተውን ማወቅ ቀጣዩን ወረርሽኝ ለመከላከል ይረዳናል” ያሉት ዶክተር ቴዎድሮስ “የኮቪድ አመጣጥን በተመለከተ ገና መደምደሚያ ላይ ስላልደረስን መረጃውን እንደሚያካፍሉ ተስፋ እናደርጋለን” በማለት ዳግም ጥያቄያቸውን አቅርበዋል።
የትራምፕ አስተዳደር የአለም ጤና ድርጅት አሜሪካ ስታቀርብ የቆየችውን ውለታ በመርሳት የአገሪቱን ጥቅም በሚጎዳ መልኩ ሲንቀሳቀስ እንደቆየ በመናገር ሲወነጅል ድርጅቱ በተቃራኒው ይህ ክስ መሰረተ ቢስ እንደሆነ ይገልጻል።
አሜሪካ እ.ኤ.አ በ1948 የዓለም ጤና ድርጅትን ስትቀላቀል በፈለገች ግዜ ከአባልነት እራሷን የማግለል መብቷን ያስጠበቀች ሲሆን ድርጅቱም ይህ በሚሆን ግዜ አገሪቱ ከአንድ አመት አስቀድሞ ቅድሚያ ማስታወቂያ እንድትሰጥ እና ለዚያ የበጀት ዓመት የመዋጮ ግዴታዋን ሙሉ በሙሉ እንድትከፍል ቅድመ ሁኔታ አስቀምጧል።
አሜሪካ በአሁኑ ሰዓት ከድርጅቱ አባልነት እራሷን ያገለለች ቢሆንም የ2024 ወይም 2025 መዋጮዋን እንዳልከፈለች እና 260 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ ዕዳ እንዳለባት የአለም ጤና ድርጅት ባወጣው መረጃ ገልጿል።












