የአለም ጤና ድርጅት ከመጠን ያለፈ ውፍረት ያለባቸው ሰዎችን ክብደት ለመቀነስ የሚያስችል ክትባት እንዲሰጥ ለመጀመሪያ ድጋፍ ሰጥቷል።
የድርጅቱ ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም “አዲሱ መመሪያ ከመጠን ያለፈ ውፍረት ወይም ኦቤሲቲ ከባድ በሽታ ነው ብሎ እውቅና መስጠቱንና ሊታከም የሚችል” መሆኑን ተናግረዋል። ክትባቱ ከመጠን ላለፈ ውፍረት በራሱ መፍትሄ እንደማይሆን የተናገሩት ዳይሬክተሩ ሚሊዮኖች ክብደታቸውን እንዲቀንሱና ተያያዥ ጉዳቶችን እንዲቀንሱ ይረዳቸዋል ብለዋል።

እንደ ድርጅቱ ከሆነ በአለም ዙሪያ አንድ ቢሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ከመጠን ያለፈ ውፍረት ተጠቂ ናቸው። እ.ኤ.አ. በ2030 ይህ አሀዝ ወደ ሁለት ቢሊዮን ከፍ ይላል ብሏል ድርጅቱ።
ጂኤልፒ-1 (GLP-1) የተባለው ይህ ክትባት ሆሮሞን በማስመሰልና የኢንሱሊንን ልቀት በመጨመር በደም ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን የመቆጣጠር እና የምግብ ፍላጎት የመቀነስ ስራ እንደሚሰራ ስካይ ኒውስ ዘግቧል። ድርጁቱ ባወጣው የመጀመሪያ የአጠቃቀም መመሪያ ነፍሰጡር ሴቶች እንዳይጠቀሙት መክሯል።












