ዱባይ፣ አቡዳቢና ዶሃና የተባሉት የአረብ ባህረሰላጤ ከተሞችና የባህሬኗ ዋና ከተማ ማናማ የአሜሪካን የጦር ሰፈሮች ባስጠለሉ ሀገራት ላይ ጥቃት እያደረሰች ባለችው ኢራን በዛሬው እለት በአዲስ ድብደባ እየተናወጡ ነው።
በጥቃቱ ሳቢያ በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ ሀገራት የአየር ክልላቸውንና ቁልፍ አየር መንገዶቻቸውን በመዝጋታቸው በ10ሺዎች የሚቆጠሩ መንገደኞች መንቀሳቀስ አልቻሉም።
ኢራን እየፈጸመች ያለችው የአጸፋ እርምጃ አድማሱን እያሰፋ ሲሆን በአረብ ኤምሬትስ ዋና ከተማ የሚገኝ የእስራኤልና የሌሎች ሀገራትን ኢምባሲዎች የከተሙበት ህንጻ ጥቃት ደርሶበታል።
በአየር መቃወሚያ የከሸፈ ሚሳይል ስብርባሪ በህንጻው ላይ መጠነኛ ጉዳት ማድረሱን የአቡ ዳቢ የመንግስት መገናኛ ብዙኻን በዛሬው እለት ዘግበዋል። የኢትሃድ ታወርም እንደዚሁ በድሮን ስብርባሪ ጉዳት እንደደረሰበት ተዘግቧል።
ኢራን በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ የአሜሪካ የጦር ሰፈሮችንና ሌሎች ተቋማትን ኢላማ ያደረገ ጥቃት የምትፈጽመው፣ እስራኤል ከአሜሪካ ጋር በመቀናጀት ያደረሰችባትን ከባድ ጥቃት ለመበቀል ነው።
እስራኤልና አሜሪካ በቅንጅት በፈጸሙት ጥቃት የኢራኑ ጠቅላይ መሪ አሊ ኻሚኒና ከፍተኛ የጦር ባለስልጣናት እንዲሁም 200 ገደማ ንጹሃን መገደላቸው የተዘገበ ሲሆን ኢራን በፈጸመችው ጥቃትም እስራኤል ውስጥ የሰው ህይወት አልፏል።
ከግጭቱ በፊት አሜሪካ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በመካከለኛው ምስራቅ ከፍተኛ ወታደራዊ ስምሪት ስታደርግ ቆይታለች። አሜሪካ ይህን ያደረገችው ኢራን በኑክሌር ጦር መሳሪያ መርሃግብሯ ዙሪያ ከስምምነት ላይ እንድትደርስ ጫኔ ለማሳደር የነበረ ቢሆንም የመጨረሻውን በኦማን የተደረገውን ጨምሮ ዲፕሎማሲያዊ ንግግሮች አልተሳኩም። በዚህ ምክንያት ትራምፕ ሲዝቱ እንደነበረው ቴህራን” መጥፎ ነገር” አጋጥሟታል።
እስራኤልና አሜሪካ የኑክሌር ጦር መሳሪያ የታጠቀች ኢራን ለህልውናቸው ስጋት ስለምትሆን መድቀቅ አለባት የሚል አቋም አላቸው።ፕሬዝዳንት ትራምፕ እንዳሉት የጥቃቱ አላማ በኢራን የአሜሪካን ሀሳብ የሚቀበል የስርአት ለውጥ ማምጣት ነው።
ቻይና፣ ሩሲያና ደቡብ አፍሪካን ጨምሮ የተወሰኑ ሀገራት እስራኤልና አሜሪካ እየፈጸሙ ያሉትን ጥቃቱ ሲያወግዙ፣ አብዛኞቹ ደግሞ ግጭቱ እንደሚያሳስባቸው መግለጫ እያሰጡ ናቸው።











