የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ የዋሽንግተን ጉብኝትን ተከትሎ አሜሪካ እና ቻይና 30 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ባላቸው ዕቃዎች ላይ ታሪፍ ለመቀነስ እና በሰው ሰራሽ እውቀት (AI) ላይ ውይይት ለመጀመር መስማማታቸውን ሁለቱም ሀገራት አስታዉቀዋል።
የታሪፍ ቅነሳው የሚተገበረዉ ከአሜሪካ ወደ ቻይና በሚላኩ የግብርና ምርቶች፣ እንጨት እና የመዋቢያ ዕቃዎች ላይ እንዲሁም ከቻይና ወደ አሜሪካ በሚገቡ አነስተኛ የቤት መሣሪያዎች፣ መጫወቻዎች እና የጌጣጌጥ ዕቃዎች ላይ መሆኑን ዋይት ሀውስ ባወጣው መግለጫ አረጋግጧል።
ዋይት ሀውስ እንደገለጸው “ሁለቱ አገራት በእያንዳንዱ አቅጣጫ 30 ቢሊዮን ዶላር የሚገመቱ መደበኛ የሆኑ (non-sensitive) ዕቃዎች በተመጣጣኝ የታሪፍ ክፍያ እንዲያልፉ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።”
በሺ እና በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ መካከል የተካሄደው የሦስት ቀን ጉባኤ አርብ ዕለት ተጠናቋል። ሺ ጂንፒንግም ትናንት ወደ ቤጂንግ ተመልሰዋል። ሁለቱ ወገኖች የንግድ ምክር ቤት ለማቋቋም እና በኩዋላ ላምፑር በተደረጉ ቀደምት ውይይቶች የተገኙ ውጤቶችን ለማስቀጠልም ተስማምተዋል።ይህ ስምምነት የመጣው ሁለቱ ሀገራት ቀደም ሲል ያደረጉትን የንግድ ስምምነት በሁለት ወራት ለማራዘም ከወሰኑ በኋላ ነው። ይህ ስምምነት በህዳር ወር ሊያበቃ እንደነበር የገለጹት የአሜሪካ ግምጃ ቤት ጸሐፊ ስኮት ቤሰንት፣ መራዘሙ የተሻለ እና ሰፊ የንግድ ስምምነት ላይ ለመድረስ ተጨማሪ ጊዜ ይሰጣል ብለዋል።

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ፣ “ይህ ታሪካዊ ጉብኝት ገንቢና የተረጋጋ የቻይና–አሜሪካ ግንኙነትን አጠናክሯል። የሁለትዮሽ ግንኙነቱን አጠቃላይ መረጋጋት ጠብቋል፣ በቻይናና አሜሪካ ግንኙነት አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ሲሆን በዓለም ሰላምና ልማት ላይ ረጅም ጊዜ የሚቆይ ተጽዕኖ ይኖረዋል።”
ሁለቱ መሪዎች ከታሪፍ ቅነሳ በተጨማሪ የሰው ሰራሽ እውቀት (AI) ቴክኖሎጂ ስለሚያስከትላቸው አደጋዎችና ስለሚያስገኛቸው ጥቅሞች ውይይት ለማካሄድ፣ እንዲሁም መረጃ ለመለዋወጥ ተስማምተዋል።የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም በዚሁ ጉዳይ ባወጣው መግለጫ፣ ቴክኖሎጂው እየተሻሻለ በሚሄድበት ጊዜ ሁለቱ ሀገራት አዳዲስ እድገቶችን የተመለከቱ ልውውጦችን ማጠናከርና የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ መስራት አለባቸው ብሏል።
ሁለቱ አገራት በተጨማሪ የእስያ–ፓሲፊክ የኢኮኖሚ ትብብር (APEC) መሪዎች ስብሰባን እና የG20 ጉባኤን በሚያስተናግዱበት ጊዜ እርስ በርሳቸው ድጋፍ ለማድረግ ተስማምተዋል። ሁለቱም መሪዎች በሌላው ሀገር በሚዘጋጁት ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት እቅድ አላቸው።
ኢራን የኑክሌር መሣሪያ ላለመገንባት የገባችውን ቃል መፈጸም እንዳለባት የተስማሙት መሪዎቹ፣ ማንኛውም ሀገር ወይም አካል በዓለም አቀፍ የውሃ መስመሮች ላይ የመጓጓዣ ክፍያ መጫን እንደሌለበት የጋራ አቋም ይዘዋል።












