ቻይና በባቡር መሰረተልማት ዝርጋታ በሰፊው ከመግባቷ በፊት ባቡር ለአብዛኛው የአፍሪካ ክፍል እንደቅንጦት ነበር የሚታየው።
አውሮፓ፣ አሜሪካና እሲያ ባቡር መጠቀም ከጀመሩ የቆዩ ሲሆን አፍሪካውያን ግን ወደ ኋላ ቀርተው ነበር። ነገርግን ቻይና በአፍሪካ ሀገራት ልክ እንደሰለጠነው አለም የባቡር ኔትወርክ መዘርጋት እንደሚቻል አሳይታለች። ቻይና በበርካታ የአፍሪካ ሀገራት በርካታ የባቡር ፕሮጀክቶችን ሰርታ አጠናቃለች።
የቻይና መንግስት ብዙ ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ላላቸው ፕሮጀክቶች ብድር በመስጠትና በመገንባት አስረክቧል።
በታሪክ እንደታየው የአፍሪካ ሀገራት ግዙፍ ብሔራዊ መሰረተልማት ለመገንባት ብድር ማግኘት ማነቆ ሆኖባቸው ቆይቷል። ይህ የሆነው አይኤምኤፍና የአለምባንክን የመሳሰሉት የምዕራባውያን አበዳሪ ተቋማት ብድር ለመስጠት ቅድመ ሁኔታዎችን ስለሚያስቀምጡ ነው።
በአንጻሩ በሀገራት የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ያለመግባት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የምትከተለው ቻይና ለበርካታ የባቡር ፕሮጀክቶች ብድር ሰጥታለች።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዝደንት የሆኑት ዶክተር ጄይሉ ኡመር የቻይና ጣልቃ ያለመግባት (non-interference) ፖሊሲና በተባበሩት መንግስታ(ተመድ) ለአፍሪካ ወግና መከራከሯ ለልማት፣ ለሰለምና ትበብር ወሳኝ እንደሆነ ገልጸዋል።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት እስከ እ.ኤ.አ 2025 ድረስ ቻይና በአፍሪካ ውስጥ 10ሺህ ኪሎሜትር የባቡር መስመር ዘርግታለች። አብዛኞቹ ፕሮጀክቶች ፈንድ የተደረጉት በቻይና ኢምፖርት ኤክስፖርት (ኤግዚም) ባንክ መሆኑ ቻይና በ21ኛው ክፍለዘመን የአፍሪካን ትስስር ለማምጣት ምን ያህል በሰፊው እንደሰራች ማሳያ እንደሆነ ይነገራል።
ዶክተር ጄሉ እንደገለጹት ቻይና በሰላም፣ በልማትና በኢኮኖሚ ዘርፎች የጀመረቻቸው መርሃግብሮች ለአፍሪካ ልማት ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
“ቻይና የአፍሪካ ሀገራትን ኢንዱሰትሪ፣ መሰረተልማትና የሰው ሀብት ልማት በመደገፍ ወሳኝ ድርሻ እየተወጣች ነው” ብለዋል ዶክተር ጄይሉ።
ቻይኒ እ.ኤ.አ. በ2013 ከአፍሪካ ህብረት አጄንዳ 2063ና አፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ጋር የሚጣጣም ‘ቤልት ኤንድ ሮድ’ (ቢአርአይ) የተባለ ፕሮግራም ይፋ ማድረጓ ይታወሳል። የባቡር መሰረተልማትን ዋና ትኩረቱ ያደረገው ቢአርአይ አስካሁን ድረስ የ53 ሀገራትን ድጋፍ አግኝቷል። ቻይና በአጠቃላይ እ.ኤ.አ ከ2000-2023, ባቡርን ጨምሮ ለአፍሪካ ለመሰረተልማት ግንባት 182 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ብደር አቅርባለች።
ይህ ሀገሪቱ ለአፍሪካ መሰረተልማት ግንባታ ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያል ተብሏል።
በቻይና ኩባንያዎች ከተገነቡትና አገልግሎት እየሰጡ ካሉት ፕሮጀክቶች መካከል የአዲስ አበባ-ጅቡቲ፣ ሞምባሳ-ናይሮቢ ስታንዳርድ ጌጅ፣ አቡጃ ካዱና የአንጎላው ቤንጉይላ የባቡር መስመሮች ይገኙበታል።


በአህጉሪቱ በግንባታ ላይ ያሉ በርካታ ፕሮጀክቶች አሉ፣ ከእነዚህ ውስጥ 20 ቢሊዮን ዶላር በጀት የተያዘለት 650 ኪሎሜትር የሚረዝመው የጊኒው ሲሚንዱ የባቡር መስመር ይገኝበታል።
በ2026ም ተጨማሪ ፕሮጀክቶች ይጀመራሉ።
የቻይና መንግስት ተቋራጭ የሆኑት ቻይና ሬልዋይ ግሩፕ (ሲአርጂ)፣ ሲሲአርሲሲና ሲአርሲሲ በመሰረተልማት ግንባታዎች ድርሻቸው ከፍተኛ ነው።
የምዕራባውያን አበዳሪዎች ብድር ለመስጠት በርካታ ቅድመ ሁኔታዎችን በሚደረድሩበት ወቅት፣ የቻይና ተሳትፎ ለአፍሪካ ሀገራት ትልቅ እድል ይዞ መጥቷል። በዚህም ሀገሪቱ በአፍሪካ የመሰረተልማት ዝርጋታ የምታደርገው ተሳትሮ አይተኬ ሆኗል።
አብዛኛዎቹ የህብረተሰብ ክፏላ ወጣት የሆነባት ከፍሪካ ይህን የሚሸከም መሰረተልማት ለመገንባት ፈጣንና ቀልጣፋ ብድር ትፈልግ ነበር፤ ቻይናም ያደረገችው ይህንኑ ነበር። ከዚህ በተጨማሪም የብሪክስ መስራች አባሏ ቻይና ተመሳሳይ አቋም ለመያዝ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ንግግሮችን እያደረገች ነው።












