በዱባይ ፖሊስ አካዳሚ በተካሄደው 25ኛው የዱባይ ማራቶን የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር ሁለት ጊዜ ተደጋግሞ ተሰምቷል። ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በወንዶችም ሆነ በሴቶች ዘርፍ ተቀናቃኞቻቸውን በመብለጥ ድል ቀንቷቸዋል።
በወንዶች ውድድር የ26 ዓመቱ አትሌት ንብረት መላክ ለመጀመሪያ ጊዜ በማራቶን ተሳትፎው 2፡04፡00 በሆነ ፈጣን ሰዓት በመግባት ድል ተቀዳጅቷል። ይህም ንብረትን በዱባይ ማራቶን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳትፈው ካሸነፉ ስድስት ተከታታይ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ተርታ አሰልፎታል።
ንብረት እስከ 35ኛው ኪሎ ሜትር ድረስ ከፊት ከነበሩ 20 ሯጮች ጋር አብሮ የቆየ ቢሆንም በመጨረሻዎቹ ኪሎ ሜትሮች ባሳየው አስደናቂ ፍጥነት ሌሎቹን በመቀደም አንደኛ ወጥቷል። ሌላኛው ኢትዮጵያዊ ያሲን ሐጂ 2፡05፡52 በሆነ ሰዓት ሁለተኛ ሲወጣ ሩዋንዳዊው ጆን ሀኪዚማና ሦስተኛ ሆኖ አጠናቅቋል።
ንብረት ከውድድሩ በኋላ ሲናገር፦
“ለዚህ ውድድር በሚገባ ተዘጋጅቼ ነበር፤ ዓላማዬም በመጀመሪያ ተሳትፎዬ ማሸነፍ ነበር። ወደፊት የዓለምን ክብረ ወሰን የመስበር ትልቅ ህልም አለኝ።”
የአንቺንአሉ ደሴ ሦስተኛ ድል
በሴቶች ዘርፍ አንቺንአሉ ደሴ ካደረገቻቸው ሦስት የማራቶን ውድድሮች ሦስቱንም በማሸነፍ ብቃቷን አሳይታለች። አንቺንአሉ የራሷን ምርጥ ሰዓት በአራት ደቂቃ በማሻሻል 2፡18፡31 በሆነ ሰዓት በአንደኝነት አጠናቃለች።
ውድድሩ እስከ መጨረሻው ሁለት ኪሎ ሜትር ድረስ ከፍተኛ ፉክክር የታየበት ቢሆንም አትሌት ሙሉዬ ደከቦ በጨጓራ ህመም ምክንያት ፍጥነቷ በመቀነሱ አንቺንአሉ 40ኛው ኪሎ ሜትር ላይ ቀድማ በመውጣት አሸንፋለች። ሙሉዬ ደከቦ በ2፡18፡43 ሁለተኛ ስትወጣ፣ ፋንቱ ወርቁ በ2፡19፡08 ሦስተኛ በመውጣት ኢትዮጵያውያን በሴቶች ዘርፍ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ያለውን ደረጃ እንዲቆጣጠሩ አስችላለች።












