ኢትዮጵያ በደቡብ ኢትዮጵያ ጅንካ ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ ከተከሰተው የማርቡርግ ቫይረስ ነጻ መሆኗን የጤና ሚኒስቴር በዛሬው እለት አውጇል።
ሚኒስቴሩ ይህን ያወጀው ባለፉት 42 ተከታታይ ቀናት በቫይረሱ የተያዘ አዲስ የመዘገበ ተጠቂ አለመኖሩን ተከትሎ ነው።
እስካሁን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 14 ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ዘጠኙ ህይወታቸው ማለፉን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ “በብዙ ስራ ምክንያት ኢትዮጵያ አሁን ከቫይረሱ ነጻ መሆኗን አረጋግጠናል” ሲሉ በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።
ቫይረሱ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ መከሰቱ የተረጋገጠው ባለፈው ህዳር ወር ነበር።












