አሜሪካ በትናንትናው እለት በቬንዙዌላ ዋና ከተማ ካራካስ ላይ ባካሄደችው እጅግ አስገራሚ ነበር በተባለው ጥቃት ፕሬዝዳንት ማዱሮንና ባለቤታቸውን ሲላ ፍሎሬስን በመያዝ ወደ ኒው ዮርክ ወስዳለች።
ፕሬዝደንት ትራምፕ ማዱሮ ከተያዙ በኋላ በሰጡት የመጀመሪያ መግለጫቸው ሰላማዊ የፖለቲካ ሽግግር እስከሚደረግ ድረስ አሜሪካ ሀገሪቱን እንደምታስተዳድር ገልጸዋል።
አሜሪካ በአንድ ጊዜ 150 ዝቅ ብለው የሚበሩ 150 ተዋጊ ሄሊኮፕተሮችን ያሳተፈ መጠነሰፊ ጥቃት የከፈተችው፣ ፕሬዝደንት ትራምፕ ማዱሮ ወደ አሜሪካ አደገኛ አደንዛዥ እጽ የሚያዘዋውር ወንጀለኛ ቡድንን ይመራሉ የሚል ክስና ማስጠንቀቂያ ካስሙ ከወራት በኋላ ነው።
በቅርቡ አሜሪካ የቬንዙዌላ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች እንዳይንቀሳቀሱ ማገዷ በሁለቱ ሀገራት መካከል የነበረውን ውጥረት እንዲያይል አድርጎት ነበር።
የአሜሪካ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ፖም ቦንዲ ማዱሮ በእጽና መሳሪያ ዝውውር በኒው ዮርክ ከተማ ክስ እንደተመሰረተባቸውና የአሜሪካ ህግ ተፈጻሚ እንደሚሆንባቸው ገልጸዋል።
አሜሪካ የሀገራት መሪዎች ስትይዝ ማዱሮ የመጀመሪያዋ አይደለም።
አሜሪካ ከበርካታ የደቡብ አሜሪካ ሀገራት ጋር ያላት ፖለቲካዊ መስጋብር በውጥረት የተሞላ ሲሆን ከዚህ በፊት የሆንዱራስና የፓናማና መሪዎችም ተመሳሳይ እጣፈንታ ገጥማቸው ነበር።
አሜሪካ እ.ኤ.አ. በ1989 የያኔውን የፓናማ መሪ ጀነራል ማኑኤል ኖሪጋን በተመሳሳይ ሁኔታ በቁጥጥር ስር አውላ ከእጽ ጋር የተያያዘ ክስ አቅርባለች። አሜሪካ በፓናማ የሚገኙ ዜጎቿን ከጥቃት ለመከላከል እንደሆነ በመግለጽ ነበር የዘመቻውን ትክክለኛነት የተከላከለችው።
አሜሪካ ኖሪጋን ልክ እንደማዱሮ ሁሉ ህገወጥ መሪ በማለት ኖሪጋ በምርጫ አሸንፌያቸዋለሁ ለሚሏቸው የተቃዋሚ እጩ እውቅና ሰጥታለች።

የቀድሞው ሆንዱራስ ፕሬዝደንት ጁዋን ኦርላንዶ ኸርናንዴዝም በአሜሪካ ኤጀንቶችና በሀገሪቱ ኃይል ተባባሪነት በመኖሪያ ቤታቸው ተያዙ። ኸርናንዴዝ እ.ኤ.አ. በ2022 ለአሜሪካ ተላፈው ከተሰጡ በኋላ ከእጽ ዝውውር ጋር በተያያዘ ክስ ጥፋተኛ ተብለው 45 አመት እስር ተፈርዶባቸዋል። ትራምፕ ባለፈው ታህሳስ ወር ኸርናንዴዝን በይቅርታ እንዲፈቱ ማድረጋቸው ተዘግቧል።

ሌላው የአሜሪካ ጥቃት የሆኑት መሪ የኢራቁ መሪ ሳዳም ሁሴን ናቸው።
አሜሪካ እ.አ.አ. በ2003 በኢራቅ ላይ በሽብር ላይ ጦርነት(war on terror) የተባለውን አጠቃላይ ጦርነት ያወጀችው በተሳሳተ መልኩ የ3000 ገደማ ሰዎችን ህይወት ከቀጠፈው የመስከረም አንዱ (9/11) የኒው ዮርክ የሽብር ጥቃት ጋር በማያያዝ ነበር። አሜሪካኖች በኢራቅ ያካሄዱትን ዘመቻ ምክያታዊ ለማድረግ ሳዳም አስጊ የሚሆን ጅምላ ጨራሽ መሳሪያ ታጥቋል ይሉ ነበር፤ ነገርግን ይህ መነሻ የሀሰት መሆኑ መጨረሻ ላይ ተረጋግጧል።
ዘመቻው ከተጀመረ ከዘጠኝ ወራት በኋላ በትውልድ ከተማው ትክሪት ጉድጓድ ውስጥ ተደብቆ የተገኘው ሳዳም በዚያው በኢራቅ ፍርድ ቤት በሰብዓዊነት ላይ በተፈጸመ ወንጀል ክስ ጥፋተኛ ተብሎ በስቅላት መቀጣቱ ይታወሳል።

አሜሪካ የሉአላዊ ሀገራትን ድንበር ጥሳ መሪ እስከመያዝ መድፈሯን በርካታ ፖለቲከኞችና ሀገራት በስጋት እየተመለከቱት ይገኛሉ።











