የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጊዲዮን ሳአር፣ ሀገራቸው ለሶማሊላንድ ሪፐብሊክ የሰጠችውን ይፋዊ የሀገርነት እውቅና ተከትሎ የመጀመሪያውን ታሪካዊ ጉብኝት በሀርጌሳ አድርገዋል። ይህ ጉብኝት እስራኤል እ.ኤ.አ ታህሳስ 26 ቀን 2025 (ታህሳስ 17 ቀን 2018 ዓ.ም) እውቅና ከሰጠች ከ10 ቀናት በኋላ የተደረገ ነው።
ሚኒስትር ጊዲዮን ሳአር በሀርጌሳ ከሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት አብዲራህማን መሐመድ አብደላሂ (ኢሮ) ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ የሁለቱን ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ ተግባራዊ ትብብር ለመቀየር በሚቻልባቸው ነጥቦች ላይ ተወያይተዋል።
በቅርቡ በሀርጌሳ እና በቴል አቪቭ ሙሉ የኤምባሲ አገልግሎት የሚሰጡ ጽሕፈት ቤቶችን ለመክፈት እና አምባሳደሮችን ለመሾም ከስምምነት ደርሰዋል። ሁለቱ ሀገራት በቀይ ባህር እና በኤደን ባህረ ሰላጤ ያለውን ደህንነት ለመጠበቅ እንዲሁም የባህር ላይ ሽብርተኝነትን ለመከላከል በመከላከያ (Defense) ዘርፍ በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል። እስራኤል በውሃ ማጣራት (Water Management)፣ በዘመናዊ ግግብርና እና በጤና ዘርፍ ለሶማሊላንድ ቴክኒካዊ ድጋፍ እንደምታደርግ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።
ፕሬዝዳንት አብዲራህማን ኢሮ ከጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የቀረበላቸውን የሀገር ጉብኝት ጥሪ የተቀበሉ ሲሆን፣ በቅርቡ ወደ እስራኤል እንደሚያቀኑ ተገልጿል።
የቀጠናው ፖለቲካዊ አንድምታ
ይህ ጉብኝት እስራኤል በአፍሪካ ቀንድ ያላትን ስትራቴጂካዊ ተፅዕኖ ለማሳደግ የወሰደችው ትልቅ እርምጃ ነው። ምንም እንኳን የሶማሊያ ፌደራል መንግስት ይህንን እርምጃ “ሉዓላዊነቴን የሚጋፋ ነው” በሚል ቢቃወመውም፣ ሶማሊላንድ ግን የእስራኤል እውቅና ለ34 ዓመታት ስታደርግ ለነበረው የነፃነት ትግል ትልቅ ድል መሆኑን እየገለጸች ትገኛለች።
ሚኒስትር ጊዲዮን ሳአር በሀርጌሳ በነበራቸው ቆይታ፣ “እስራኤል በዲሞክራሲያዊ መንገድ ለሚመሩ እና ሰላምን ለሚፈልጉ የቀጠናው ሀገራት ሁሌም አጋር ናት” ሲሉ የሶማሊላንድን የሰላም ጉዞ አድንቀዋል።











