በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል እየተካሄደ ባለው ጦርነት ኬንያውያን ተሳትፎ እንዲያደርጉ በሕገ-ወጥ መንገድ ሲመለምል የነበረ ግለሰብ በኬንያ የፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር መዋሉ ተነገረ።
ግለሰቡ ስራ አጥ የሆኑ ኬንያውያን ወጣቶችን ኢላማ በማድረግ በሩሲያ በኩል ተሰልፈው እንዲዋጉ ከፍተኛ ወርሃዊ ክፍያ እና ጥቅማጥቅሞችን ቃል በመግባት ሲያታልል እንደነበር ተገልጿል። ይህ ግለሰብ ከዓለም አቀፍ የሰዎች አታላዮች እና የሕገ-ወጥ የሰዎች አጓጓዦች ጋር ግንኙነት እንዳለው የኬንያ ብሔራዊ የመረጃ አገልግሎት (NIS) ጠቁሟል።
ኦምዋምባ “ግሎባል ፌስ ሂውማን ሪሶርስ” በተባለ የቅጥር ድርጅት ስም ወጣቶችን በሩሲያ፣ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እና በቱርክ ከፍተኛ ክፍያ የሚያስገኝ የሲቪል ስራ እና እስከ 1.2 ሚሊዮን የኬንያ ሺሊንግ የሚደርስ ጉርሻ (Bonus) እንደሚሰጣቸው ቃል በመግባት ሲያታልል ቆይቷል። ነገር ግን ተመልማዮቹ ሩሲያ ከገቡ በኋላ ፓስፖርታቸው ተቀምቶ በግዳጅ ወደ ጦር ግንባር እንዲሰማሩ መደረጋቸው ተነግሯል።

ምልመላው የሚካሄደው “በሩሲያ ከፍተኛ ክፍያ የሚያስገኝ የጥበቃ ስራ አለ” በሚል የሐሰት ወሬ ሲሆን ወጣቶቹ ሩሲያ ከገቡ በኋላ ግን በቀጥታ ወደ ጦር ግንባር እንደሚሰማሩ ተረጋግጧል።
ዘገባዎች እንደሚያመለክተው ከ1,000 በላይ ኬንያውያን በዚህ መንገድ ተመልምለው ወደ ጦርነቱ ገብተዋል። ከእነዚህም መካከል፦
- 89ኙ በአሁኑ ወቅት በጦር ግንባር ላይ ይገኛሉ፤
- 39ኙ በደረሰባቸው ከባድ ጉዳት ሆስፒታል ገብተዋል፤
- 28ቱ የደረሱበት ሳይታወቅ የጠፉ ሲሆን ቢያንስ የአንድ ኬንያዊ ሞት ተረጋግጧል።
ኬንያውያን በሌላ ሀገር ጦርነት ውስጥ ገብተው ሕይወታቸውን እንዳያጡ የኬንያ መንግስት በአውሮፕላን ማረፊያዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ ጀምሯል።
በቅርቡ የወጡ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት ከ1,000 በላይ ኬንያውያን በተለያዩ መንገዶች ተታለው በጦርነቱ ውስጥ ተሳትፎ እያደረጉ ይገኛሉ።
ይህ በቁጥጥር ስር የዋለው ግለሰብ መያዝ በአፍሪካ ቀንድ እና በምስራቅ አፍሪካ ወጣቶችን ለጦርነት የሚመለምሉ ድብቅ ስርአቶችን ለማጋለጥ ትልቅ በር እንደሚከፍት ተስፋ ተጥሎበታል።
አፍሪካውያን እንዴት ተታለው በሩሲያ በኩል ለዩክሬን ጦርነት እንዲሳተፉ እንደሚደረጉ የቀረበውን ዝርዝር ዘገባ ያንብቡ።











