በኒጀር መዲና ኒያሜ በሚገኘው ዲዮሪ ሃማኒ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ ለደረሰው ጥቃት የሀገሪቱ ወታደራዊ መንግሥት ፈረንሳይን እና ሁለት ጎረቤት ሀገራትን ተጠያቂ አደረገ።
ጥቃቱ የተፈጸመው ረቡዕ ጥር 21 ቀን 2018 ዓ.ም (እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ጃንዋሪ 29) ሌሊት ላይ ነበር። በሞተር ሳይክል የተጫኑና በከባድ መሣሪያዎች የታጠቁ ታጣቂዎች በአውሮፕላን ማረፊያው አቅራቢያ የሚገኘውን ቁጥር 101 የአየር ኃይል ወታደራዊ ካምፕን ኢላማ አድርገው ጥቃት ሰንዝረዋል።
በወቅቱ ከፍተኛ የተኩስ ድምፅና ፍንዳታ የተሰማ ሲሆን ጥቃቱ ለሁለት ሰዓታት ያህል ቆይቷል። በኤርፖርቱ ቅጥር ጊቢ ውስጥ የነበሩ ሲቪል አውሮፕላኖች ላይ ጉዳት ሲደርስ ጥቃቱን ለመከላከል በተደረገው ግብግብ 20 የሚሆኑ አጥቂዎች መገደላቸውንና 11 መማረካቸውን የኒጀር መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል። በጥቃቱ 4 የኒጀር ወታደሮችም ቆስለዋል።
የኒጀር ወታደራዊ መሪ ጄኔራል አብዱራህማን ቲያኒ በመንግሥት ቴሌቪዥን ቀርበው ባደረጉት ንግግር ፈረንሳይን፣ ቤኒንን እና ኮትዲቩዋርን በጥቃቱ አቀነባባሪነት ከሰዋል።
ጄኔራል ቲያኒ በንግግራቸው፦
“የእነዚህ ቅጥረኞች ደጋፊ የሆኑትን ኢማኑኤል ማክሮን (የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት)፣ ፓትሪስ ታሎን (የቤኒን ፕሬዝዳንት) እና አላሳን ዋታራ (የኮትዲቩዋር ፕሬዝዳንት) እናስታውሳቸዋለን፤ የእነሱን ጩኸት ሰምተን በቅተናል አሁን ደግሞ የእኛን ጩኸት ለመስማት ይዘጋጁ” ብለዋል።
ወታደራዊው መሪ ለዚህ ክሳቸው ግልጽ ማስረጃ ባያቀርቡም ከተገደሉት አጥቂዎች መካከል አንደኛው የፈረንሳይ ዜግነት ያለው ሰው መሆኑን የመንግሥት ሚዲያዎች ዘግበዋል። ጄኔራሉ ጥቃቱን በመመከት ረገድ ለረዱአቸው “የሩሲያ አጋሮች” ምስጋና አቅርበዋል።
ይህ ክስ ቀደም ሲልም ከፈረንሳይ ጋር ግንኙነቷን ያቋረጠችው ኒጀር ከጎረቤቶቿ ቤኒን እና ኮትዲቩዋር ጋርም ያላት ግንኙነት ይበልጥ እንዲሻክር አድርጎታል። የኒጀር ባለሥልጣናት እነዚህ ሀገራት “የፈረንሳይ ተላላኪዎች ናቸው” በማለት በተደጋጋሚ ይከሷቸዋል።












