የሩሲያና ዩክሬን ተደራዳሪዎች ወሳኝ የሆነውን የግዛት ጉዳይ ለመፍታት በአረብ ኤምሬትስ አቡዳቢ ከትናንት ጀምሮ እየተደራደሩ ይገኛሉ።
በድርድሩ እስካሁን የተገኙ መፍትሄዎች አለመኖራቸው የተገለጸ ሲሆን ሩሲያም እያካሄደች ያለውን መጠነሰፊ የአየር ጥቃት በማጠናከር ዩክሬን አራት አመታትን እያገባደደ ባለው ጦርነት ውስጥ የከፋ የኃይል ቀውስ ውስጥ እንድትገባ አድርጋለች።
ኪቭ ጦርነቱን ለማስቆሞ የሚያስችል ስምምነት ላይ እንድትደርስ በአሜሪካ ጫና እየተደረገባት ሲሆን ሞስኮ ጦርነቱን የምታቆመው ኪቭ ምስራቃዊ የኢንዱስትሪ ቀጠና የሆነውን ዶምባስን አሳልፋ ከሰጠታች ብቻ እንደሆነ እየገለጸች ነው።
የሩሲያ፣ የዩክሬንና የአሜሪካ ባለስልጣናትን ባካተተውና ዛሬ እንደሚጠናቀቅ በተነገረለት የሶስትዮሽ ድርድር ላይ የግዛት ይገባኛል ግጭት ዋና ጉዳይ እንደሆነ የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ተናግረዋል።
“ሩሲያ የጀመረችውን ጦርነት ለማቆም ዝግጁ መሆን አለባት” ያሉት ዘለንስኪ ከዩክሬን ተደራዳሪዎች ጋር መረጃ እየተለዋወጡ መሆናቸውንና ከአርቡ ድርድር የተገኘውን ውጤት ለመናገር ጊዜ ገና መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።
ይህ ድርድር የተጀመረው ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ በስዊዘርላንድ ዳቮስ በተካሄደው የአለም የኢኮኖሚ ጉባኤ ላይ ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር ከተገናኙ ከአንድ ቀን በኋላ ነው።
ዩክሬን ግዛት አሳልፎ መስጠትን እጅ እንደመስጠት የምትቆጠረው ስለሆነ እንደምትስማማ ስትገልጽ፣ ሩሲያ በበኩሏ ዶምባስን ካልጠቀለለች ጦርነቱን እንደማታቆሞ በተደጋጋሚ አቋሟን አንጸባርቃለች።
የፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደር ግጭቱን ለመፍታት ፕሬዝዳንት ፑቲንን በአካል እስከማግኘት የደረሰ ጥረት ቢያደርጉም፣ እስካሁን አልተሳካላቸውም።













