ሶማሊያ በቅርቡ በሞቃዲሾ ከዲሴምበር 25–26፣ 2025 (ታኅሣሥ 16-17፣ 2018 ዓ.ም) የአካባቢ ምርጫዎችን አካሂዳለች። ለአውራጃ ምክር ቤቶች የተካሄደው ምርጫ “የአንድ ሰው፣ አንድ ድምጽ” ቀጥተኛ ምርጫን ከግማሽ ምዕተ አመት በሗላ ለመጀመሪያ ግዜ እውን ያደረገ ነበር። ይህም ሶማሊያ ቀጥተኛ የዜጎች ምርጫን ለመመለስ የወሰደችው ታሪካዊ እርምጃ ሲሆን መሀመድ ዚያድ ባሬ ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው በፊት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1969 የተካሄደው ምርጫ የመጨሻው ቀጥተኛ በዜጎች ተሳትፎ የተካሄደ ምርጫ ነበር።
በሞቃዲሹ የዚህ ሳምንት ምርጫ ቀናት፥ የተሽከርካሪ መንገዶች፣ አውሮፕላን ማረፊያው ፣ወደብ እና ብዙ የንግድ ድርጅቶች ለጊዜው ተዘግተው ውለዋል። በዋና ከተማው የሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎችን ለመጠበቅ ወደ 10,000 የሚጠጉ የጸጥታ አባላት መሰማራታቸውንም የምርጫ ኮሚሽኑ አስታውቋል።
ሶማሊያ በጎሳ ላይ ከተመሰረተው ቀጥተኛ ያልሆነ የፖለቲካ ምርጫ ስርዓት ወደ ሁለንተናዊ ምርጫ(universal suffrage) ስትሸጋገር እነዚህ የአካባቢ ምርጫዎች እንደ ሙከራ እና የሰፊ ዲሞክራሲያዊ ማሻሻያ እርምጃዎች ተደርገው ይወሰዳሉ። ለዓመታት በጎሳ ላይ የተመሰረተው የምርጫ ስርዓት ሙስናን እንደሚያስፋፋ፥ የተራ ዜጎችን ፍላጎት ማንጸባረቅ እንደማይችል እና በችሎታ ሳይሆን በጎሳ ድልድል ላይ ያተኮረ አስተዳደርን እንደሚያበረታታ ሲገለጽ ቆይቷል።

አንዳንድ ተቃዋሚዎች ምርጫው የዜጎች ተሳታፊነትን እውን በማድረግ ረገድ ትልቅ ለውጥ ያሳየ ቢሆንም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ግን በቂ እድል እንዳልተሳጣቸው ይናገራሉ። በአገር ደረጃ ይህን ቀጥተኛ ምርጫ ለማካሄድም በቅድሚያ አልሸባብ በብዛት ተቆጣጥሯቸው ባሉ አከባቢዎች ላይ የነገሰውን የሰላም እና ጽጥታ ሁኔታ ማሻሻል እንደሚቀድም በመግለጽ፥ የሚሻለው እስካሁን የቀጠለውን እና መረጋጋት በሌለበት ሁኔታም ቢሆን ሰፊውን የሶማሊያ ማህበረሰብ(በጎሳ መሰረት ቢሆንም) የሚያሳትፈውን ቀጥተኛ ያልሆነ ምርጫ ወደ ማካሄዱ መመለስ እንደሆነ ይናገራሉ።
እ.ኤ.አ. በ 2024 የወጣው አዲስ የምርጫ ህግ በሚቀጥለው ዓመት እንደሚካሄድ ከሚጠበቀው የፌዴራል ምርጫ በፊት ሁለንተናዊ ምርጫን ወደነበረበት ለመመለስ የመጀመሪያውን ቀጥተኛ ምርጫ በሞቃዲሹ ከተማ እውን ማድረግ ችሏል። ሆኖም ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ ከአንዳንድ የተቃዋሚ መሪዎች ጋር በደረሱት ስምምነት፥ ህግ አውጪዎች በ2026 በቀጥታ የሚመረጡ ሲሆን ፕሬዚዳንቱ ግን በፓርላማ መመረጡን ይቀጥላል።
አልሸባብ ሰፊውን የሶማሊያ ገጠራማ አካባቢዎችን መቆጣጠሩን እና በዋና ዋና የህዝብ ማእከላት ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት በመጥቀስ አገሪቱ በአገር አቀፍ ደረጃ ህዝባዊ ድምጽ ለመስጠት የሚያስችል አስተማማኝ አቅም ያላት ስለመሆኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጥርጣሬን ያሰማሉ።












