በለፉት ሳምንታት በስደተኞች ላይ የከፋ እርምጃ እየወሰደ ያለው በዶናልድ ትራምፕ የሚመራው የአሜሪካ አስተዳደር የዲቪ ሎተሪን በማቋረጥ የተስፈኛ ስደተኞችን ህልም አጨልሞታል።
የደህንነት ስጋትን እንደምክንያት የምትጠቅሰው አሜሪካ በበርካታ ሀገራት ላይ የጉዞ እገዳም መጣሏ ይታወሳል።
ብዙዎች ህይወታቸውን ለመቀየር በማለም አሜሪካ መግባት ይፈልጋሉ፤ ነገርግን ጸረ-ስደተኛ አቋም ያላቸው ፕሬዘዳንት ትራምፕ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ በተለይም በቅርቡ ለመሄድ የሚያልሙትን ይቅርና ቀደም ብለው የሄዱትንም ስደተኞች እረፍት የሚነሳ ህገ እየወጣ ይገኛል።
አሜሪካ ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ ካለው የውስጥ ግጭት ጋር በተያያዘ በአሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በአስገዳጅ ሁኔታ ወደ ሀገራቸው እንዳይባረሩ ተሰጥቷቸው የነበረውን ከለላ አንስታለች። ፕሬዚዳንት ትራምፕ በስደተኞች ላይ እያሳለፉ ያለው ውሳኔ እጅግ የከፋ ነው፤ በሶማሊያ ስተደኞች ላይ ያሰሙት ስድብ እጅግ መነጋገሪያ ነበር።
የዲቪ ሎተሪ መቋረጥ ወደ አሜሪካ የመግባትን እድል የበለጠ እንዲጠብ ያደርገዋል።
የአሜሪካ የሀገር ውስጥ ደህንነት ኃላፊ ክሪስቲ ኖይም በዶናልድ ትራምፕ ትዕዛዝ መሰረት በብራውን ዩኒቨርሲቲ ግድያ ተጠርጣሪ ጥቅም ላይ የዋለው የዲቪ ቪዛ በአስቸኳይ ኢንዲቋረጥ አድርግናል ብለዋል።
በብራውን ዩኒቨርስቲ ግድያ የተጠረጠረው የ 48 አመቱ ፖርቹጋላዊ በ2017 በዲቪ ቪዛ ወደ አሜሪካ የገባ መሆኑን ኖይም ጠቅሰዋል።
“እንዲህ አይነት አደገኛ ሰው ወደ ሀገራችን እንዲገባ መፈቀድ አልነበረበትም” ያሉት ኖይም ባለፈው ሳምንት በብራውን ዩኒቨርሲቲ በተፈጠረው ጅምላ ግድያ ሁለት ሰዎች መገደላቸውንና ዘጠኝ ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን ገልጸዋል።
የአሜሪካ ዜግነት እና የኢምግሬሽን አገልግሎት መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ በየአመቱ 50ሺ ስደተኞች በዲቪ ቪዛ ወደ አሜሪካ ይገባሉ።











