የአሜሪካ የአፍሪካ ዕዝ (AFRICOM) አዛዥ ጄነራል ዳግቪን አር.ኤም. አንድርሰን (General Dagvin R.M. Anderson) በአዲስ አበባ በነበራቸው ቆይታ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ከአሜሪካ አምባሳደር ጋር ያደረጉትን ውይይት አስመልከተው የሰጡት አስተያየት በሱዳን እያጋጠመ ያለው ቀውስ የት ድረስ አሳሳቢ እንደሆነ እና መፍትሔውም ምን እንደሆነ ግልጽ ማሳያ ነው።
ጄነራል አንድርሰን በሱዳን እየሆነ ያለው ነገር አሳዛኝ (Tragedy) መሆኑን በመግለጽ የችግሩ ተፅዕኖ በሱዳን ወሰን ብቻ ሳይወሰን መላውን ምስራቅ አፍሪካ ቀጣና እየጎዳ እንደሚገኝ አስመርተውበታል።

የኢትዮጵያ ሚና
ጄነራል አንድርሰን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከያዟቸው ዋነኛ አጀንዳዎች መካከል የሱዳን ጉዳይ ቀዳሚው እንደነበር ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ከአጎራባች ሀገርነቷ እና ከቀጣናዊ ተፅዕኖዋ አንጻር ለሱዳን ቀውስ ዘላቂ መፍትሔ እና ወደፊት የሚኬድበትን መንገድ መፈለግ ትልቅ ትኩረት የሰጠችው ጉዳይ መሆኑን የአፍሪኮም አዛዥ ንግግር ያረጋግጣል።
እንደ ጄነራል አንድርሰን ማብራሪያ፣ የሱዳን ሁኔታ እጅግ ውስብስብ (Complex) በመሆኑ የችግሩ መፍትሔ የአንድ ሀገር ወይም የአንድ ወገን ጥረት ብቻ ሊሆን አይችልም። የችግሩን ስፋትና ውስብስብነት የሚመጥን መፍትሔ ለማምጣት የቀጣናው ሀገራት (Regional Players) ንቁ ተሳትፎ እና የጋራ አቋም፣ የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ (International Community) የተቀናጀ ድጋፍ እና ዲፕሎማሲያዊ ጥረት በአንድ ላይ እንደሚያስፈልግ አፅንኦት ሰጥተዋል።
ከሁሉም በላይ ግን የቱንም ያህል የቀጣናው እና የዓለም አቀፍ አካላት ድጋፍ ቢኖር ዘላቂ መፍትሔ ሊመጣ የሚችለው ከራሳቸው ከሱዳናውያን እንደሆነ ጄነራል አንድርሰን አብራርተዋል።
የአፍሪኮም አዛዡ ባደረጉት ጥሪ የሱዳን ህዝብ እና ባለድርሻ አካላት ከግጭትና ከጦርነት አማራጭ በመውጣት የጋራ መፍትሔ ለማስገኘት በአንድነት መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። ጦርነትና ግጭት መፍትሔ እንደማያመጣ ጠቁመው፣ ውይይትና የጋራ ጥረት ብቻ ቀውሱን እንደሚያበቃው ገልጸዋል።












