ለብዙ አመታት የቻይናና ኢትዮጵያ የኃይል ዘርፍ ትብብር በዋናነት በኃይል ማመንጫ ግድቦች፣ በኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች እና በመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ ላይ ያተኮረ ነበር። አሁን ላይ ይህ ሁኔታ በእጅጉ ተቀይሯል።
ኢትዮጵያ ውስጥ በቻይና ድጋፍ የተሰሩ የነፋስ እና የጸሀይ ሀይል ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ኃይል ማመንጨት ጀምረዋል። 12ዐ ሜጋዋት የሚያመነጨው የንፉስ ኃይል ፕሮጀክት በቻይና ድጋፍ ከተሰሩት የንፋስ ኃይል ማመንጫዎች በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው።
የቻይና ኩባንያዎች በታዳሽ ኃይል ዘርፍ እያደረጉ ያሉት ኢንቨስትመንትና በኑክሌር ኃይል መስክ የተመሠረተው ስትራቴጂካዊ አጋርነት፣ ኢትዮጵያ የአስተማማኝ ኃይል ባለቤት እንድትሆን የሚያስችል ነው። በኑክሌር ኃይል ማመንጫ ዘርፍ የሚደረገው ትብብር፣ ለኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ አቅም ይፈጥርላታል። ከኑክሌር የሚመነጨው ኃይል ወደ ብሔራዊ ቋት(National Grid) የሚገባውን የኃይል መጠን ይጨምረዋል። ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ ወደ ጎረቤት ሀገራት የምትልከው የኃይል መጠን በመጨመር፣ ገቢዋን እንድታሳድግ አስተዋጽኦ አለው ማለት ነው። ስለዚህ ኑክሌር፣ የኃይል ምንጭን ከማስፋት ባለፈ ኢትዮጵያ ለሀገር ውስጥ ልማት አስተማማኝ ኃይል እንድታቀርብ እንዲሁም ሽያጭ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ እንድታገኝ የሚረዳ ኢንቨስትመንት ነው።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከፍተኛ የታዳሽ ኃይል ሀብት ካላቸው ሀገሮች አንዷ ነች። ሀገሪቱ ያላትን የውኃ፣ የንፋስ እና የፀሐይ ኃይል ሀብት በሚገባ ከተጠቀመችበት የአፍሪካ የታዳሽ ኃይል ማዕከል የመሆን እድሏ ሰፊ ነው። ይህን እምቅ አቅም ወደ ተረጋጋና አስተማማኝ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ለመቀየር ኢንቨስትመንት፣ ቴክኖሎጂ፣ የሰለጠነ የሰው ኃይል እና ጠንካራ ተቋማት ያስፈልጋሉ። ከዚህ በተጨማሪም ከግንባታ ውሎች በላይ ዘላቂ የሆኑ የረጅም ጊዜ አጋርነቶችም እንዲሁ አስፈላጊ ናቸው።
በዚህ ሂደት ውስጥ የቻይና ሚና በየጊዜው እየሰፋ መጥቷል። የቻይና ኩባንያዎች የሰለጠኑ ባለሙያዎችንና መሳሪያ በማቅረብ እንዲሁም በግንባታ በሰፊው እየተሳተፉ ይገኛሉ። በዶንግፋንግ ኤሌክትሪክ የተገነባው የአይሻ የንፋስ ኃይል ፕሮጀክት ለአዲስ አበባ–ጅቡቲ የባቡር መስመርና በዙሪያው ላሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ታዳሽ ኃይል በማቅረብ ለታዳሽ ኃይል ለኢንዱስትሪ፣ ለሎጂስቲክስ እና ለኢኮኖሚ ዕድገት ያለውን ቀጥተኛ አስተዋፅኦ አሳይቷል። በተመሳሳይ የሚንግያንግ ስማርት ኢነርጂ 8.4 ጊጋዋት የሚደርስ የታዳሽ ኃይል ፕሮጀክቶች ፈቃድ ማግኘቱ በኢትዮጵያ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ላይ ያለውን እምነት ያንጸባርቃል። በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብም የቻይና ኩባንያዎች ያላቸው ተሳትፎ የሀገሪቱን የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ለማጠናከር እየሰጡት ያለውን ድጋፍ ያሳያል።

ከሁሉ የበለጠ ትኩረት የሚስበው ግን በኑክሌር ኃይል ዘርፍ የተጀመረው አዲስ ትብብር ነው። ለአንዳንዶች ኢትዮጵያ አሁንም በማደግ ላይ ያለች ሀገር (developing country) ስለሆነች ይህ እርምጃ ፈጣን ሊመስል ይችላል። ነገር ግን የኑክሌር ትብብር ማለት ሬአክተሮችን መገንባት ብቻ አይደለም። ሳይንሳዊ ምርምር፣ የኑክሌር ደህንነት፣ በሕክምናና በግብርና የሚውሉ ቴክኖሎጂዎች፣ የቁጥጥር ስርዓቶች፣ እንዲሁም የመሐንዲሶችና የቴክኒሻኖች ሥልጠናን ያካትታል። በመሆኑም ይህ በመሠረተ ልማት ብቻ ሳይሆን በእውቀትና በተቋማት ላይ የሚደረግ ኢንቨስትመንት ነው።
የዚህ ትብብር ትርጉሙ ግልጽ ነው። ኢትዮጵያ የማኑፋክቸሪንግ፣ የዲጂታል ኢኮኖሚ እና የኢንዱስትሪ ልማት ያላት ትልቅ እቅድ የተረጋጋና ተመጣጣኝ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ከሌለ ሊሳካ አይችልም።”በኢትዮጵያ የተመረተ (Made in Ethiopia)” የሚለውን ራዕይ ለማሳካት የኃይል ዋስትና ወሳኝ መሠረት ነው። ታዳሽ ኃይል በተመሳሳይ ጊዜ በከርሰ ምድር ነዳጅ ላይ ያለውን ጥገኝነት ለመቀነስና የአየር ንብረት ግቦችን ለማሳካት አስፈላጊ ነው። ሀገራቱ በታዳሽ ኃይል ዘርፍ የሚያደርጉት ትብብር፣ በተለይም በኮፕ28 (COP 28) በአረብ ኢምሬትስ ለተደረሰው ወደ ታዳሽ ኃይል ፍጆታ የመሸጋገር ስምምነት ነጥቦች ተገዥ ስለመሆናቸው ተግባራዊ ምሳሌ ነው። ሀገራት በተናጠልም ይሁን በቡድን በታዳሽ ኃይል ላይ የሚያደርጉት ኢንቨትመንት አለምአቀፍ ድጋፍ የሚቸረው ነው። ቻይና ለኢትዮጵያ ወይም ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት እየሰጠች ያለው ድጋፍ ኢኮኖሚ ትብብር ከማጠናከሩ በተጨማሪ አለምአቀፍ የአየር ንብረት ፕሮቶኮሎችን ለመፈጸም ጠቃሚ ነው።
ቻይና ፋይናንስን፣ ቴክኖሎጂን፣ የክህሎት ልማትን እና ተቋማዊ ትብብርን በማጣመር ድጋፏን የምትቀጥል ከሆነ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀዳሚ የታዳሽ ኃይል ማዕከል ለመሆን በተሻለ ሁኔታ ትቀርባለች። ይህም የቻይና እና የአፍሪካ ትብብር ከመሠረተ ልማት ግንባታ ወደ ዘላቂና የጋራ ልማት እየተሸጋገረ መሆኑን የሚያሳይ ጠንካራ ምሳሌ ይሆናል።










