የሰው ልጅ ታሪክ ለዘመናት በወንዶች ብልጫ ቢጻፍም አሁን ግን ሰማዩም ሆነ ጨረቃ የሴቶችን ድምፅና ጥበብ ማስተናገድ ጀምረዋል።
በአሁኑ ወቅት የአርቴሚስ 2 (Artemis II) ተልዕኮ አካል በመሆን ወደ ጨረቃ ምህዋር በመጓዝ ላይ የምትገኘው ክርስቲና ኮክ (Christina Koch) የዓለምን ትኩረት ስባለች። ክርስቲና ቀደም ሲል በጠፈር ላይ ለ328 ቀናት በመቆየት የሴቶችን የቆይታ ሪከርድ የሰበረች ስመ-ጥሩ ጠፈርተኛ ናት። ዛሬ ደግሞ ወደ ጨረቃ በማቅናት “የመጀመሪያዋ ሴት የጨረቃ ተጓዥ” ለመሆን ታሪካዊ እርምጃዋን ጀምራለች።
ክርስቲና ኮክ ማነች?
ክርስቲና ኮክ በጠፈር ምርምር ታሪክ ውስጥ ስሟን በደመቀ ሁኔታ ያስመዘገበች ድንቅ ሳይንቲስት ናት። በአሁኑ ወቅት በአርቴሚስ 2 ተልዕኮ ወደ ጨረቃ በማምራት ላይ የምትገኘው የዚች ታላቅ ሴት የኋላ ታሪክ ለብዙዎች አርአያ የሚሆን ነው።
ክርስቲና የተወለደችው እ.ኤ.አ. ጥር 29 ቀን 1979 በሚቺጋን ግዛት ግራንድ ራፒድስ ሲሆን ያደገችው ግን በሰሜን ካሮላይና ጃክሰንቪል ነው። ገና በሕፃንነቷ የጠፈር ተመራማሪ (Astronaut) የመሆን ከፍተኛ ፍላጎት ነበራት። ገና በመዋለ ሕፃናት (Kindergarten) እያለች አስተማሪዎቿን “ጠፈርተኛ መሆን እፈልጋለሁ” ትል እንደነበር ትናገራለች።

በልጅነቷ የበጋ ወቅት እረፍቷን በሚቺጋን በሚገኘው የቤተሰቧ የእርሻ ቦታ የምታሳልፍ ሲሆን ይህም ለከባድ ሥራና ለተግዳሮቶች ያላትን ፍቅር እንዳሳደገው ትናገራለች።
ክርስቲና በሳይንስና በቴክኖሎጂ ያላት ብቃት እጅግ ከፍተኛ ሲሆን በትምህርቷም እጅግ ስኬታማ ነበረች። በሰሜን ካሮላይና የሳይንስና የሒሳብ ትምህርት ቤት (North Carolina School of Science and Mathematics) ተምራለች።
በሰሜን ካሮላይና ስቴት ዩኒቨርሲቲ (NC State University) የሦስት ዲግሪዎች ባለቤት ናት፦
- በኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ (B.S. in Electrical Engineering) – 2001
- በፊዚክስ (B.S. in Physics) – 2002
- በኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ የማስተርስ ዲግሪ (M.S. in Electrical Engineering) – 2002
በጠፈር ተመራማሪነት ከመመረጧ በፊት በተለያዩ የዓለም ክፍሎች (ከጋና እስከ አንታርክቲካ) በምርምርና በሳይንስ ሥራዎች ላይ ተሳትፋለች። እንዲሁም በቅርቡ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ተሰጥቷታል።

የሥራ ልምድ እና ወደ ናሳ (NASA) ጉዞ
የመጀመሪያ ሥራዋን የጀመረችው በናሳ የጎዳርድ የጠፈር በረራ ማዕከል (Goddard Space Flight Center) በኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ነበር።
አስቸጋሪ አካባቢዎች ምርምር በደቡብ ዋልታ (Antarctica) ለሦስት ዓመታት በምርምር ጣቢያዎች ሰርታለች። እዚያም በእሳት አደጋ መከላከልና በበረዶ ላይ የነፍስ አድን ቡድን አባል ሆና አገልግላለች። ይህ ልምድ በጠፈር ላይ ለሚገጥሙ ፈታኝ ሁኔታዎች ትልቅ ዝግጅት ሆኖላታል።
እ.ኤ.አ. በ2013 ከ6,000 በላይ የጠፈርተኛነት ምርጫ አመልካቾች መካከል ተመርጣ 21ኛው የናሳ የጠፈርተኞች ቡድን አባል ሆናለች።
ታሪካዊ ስኬቶች
በጠፈር ላይ ለ328 ተከታታይ ቀናት በመቆየት የዓለምን ሪከርድ ሰብራለች። ከጄሲካ ሜር ጋር በመሆን የመጀመሪያውን በሴቶች ብቻ የተመራ የጠፈር ላይ የእግር ጉዞ (Spacewalk) አከናውናለች።

ታሪካዊ ትውስታ፦ የመጀመሪያዋ የሮኬት ሳይንቲስት “ሜሪ ሸርማን ሞርጋን”
የዛሬዎቹ የአርቴሚስ ሴቶች ስኬት መሠረቱ የተጣለው ከበርካታ አሥርተ ዓመታት በፊት ነው። በጠፈር ምርምር ታሪክ ውስጥ ስሟ ብዙ ባይነሳም ሜሪ ሸርማን ሞርጋን (Mary Sherman Morgan) የመጀመሪያዋ ሴት የሮኬት ነዳጅ ሳይንቲስት ተደርጋ ትጠቀሳለች።
እ.ኤ.አ. በ1950ዎቹ አሜሪካ የመጀመሪያዋን ሳተላይት (Explorer 1) ወደ ጠፈር ለማምጠቅ ስትሞክር በተደጋጋሚ ሳይሳካላት ቀርቶ ነበር። ችግሩ የነዳጅ አቅም ማነስ ነበር። ሜሪ ሸርማን በወቅቱ “Hydyne” የተሰኘ አዲስና ከፍተኛ ኃይል ያለው የሮኬት ነዳጅ በመፍጠር አሜሪካን ወደ ጠፈር ፉክክር እንድትገባ አድርጋለች።
በወቅቱ በዘርፉ ሴት መሆን ብቻ ሳይሆን ሳይንቲስት ሆኖ መገኘት እጅግ ብርቅና ፈታኝ ነበር። ሜሪ ግን በዝምታና በጥበብ የሰው ልጅን ወደ ሰማይ ያመጠቀውን ነዳጅ ቀምማ አልፋለች።













