“መከራ ሲመጣ ተያይዞ ነው” እንዲሉ፤ በኃያላን ሀገራት የሚሳኤል ድብደባ እየተናወጠች የምትገኘው ኢራን ዛሬ ደግሞ ሌላ የተፈጥሮ አደጋ አስተናግዳለች። በአሜሪካ እና በእስራኤል የተቀናጀ ጥቃት መሪዎቿንና ወታደራዊ ተቋማቷን ያጣችው ቴህራን ድንገተኛና ኃይለኛ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከስቶባታል።
በሀገሪቱ ደቡባዊ እና መካከለኛ ክፍሎች ኃይለኛ የመሬት መንቀጥቀጥ በሬክተር ስኬል 5.8 ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን በቴህራን እና በዙሪያዋ ባሉ ከተሞች ከፍተኛ ድንጋጤን ፈጥሯል።
ይህ ክስተት በኢራን ሕዝብ ላይ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንደሚባለው ሆኖባቸዋል። በአንድ በኩል ከሰማይ የሚዘንበው ቦምብ በሌላ በኩል ደግሞ ከእግር በታች የሚናወጠው መሬት ሀገሪቱን ወደ ማይወጣው ምስቅልቅል ውስጥ ከተዋታል።
አንዳንድ ወታደራዊ ተንታኞች እንደሚሉት ከሆነ፣ አሜሪካ እና እስራኤል የኢራንን የመሬት ውስጥ የኑክሌር ተቋማት ለማውደም የተጠቀሙባቸው “ባንከር በስተር” (Bunker Buster) የተሰኙ ግዙፍ ቦምቦች ያስከተሉት ንዝረት ለመሬት መንቀጥቀጡ መከሰት ምክንያት ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት አላቸው።
መንቀጥቀጡ የተከሰተው የኢራን የኑክሌር ተቋማት በሚገኙባቸው አካባቢዎች በመሆኑ የጨረር መፍሰስ አደጋ ሊያጋጥም ይችላል የሚል ስጋት በዓለም አቀፍ ደረጃ አይሏል።
በአየር ድብደባው ምክንያት የፈራረሱ ሕንፃዎች ሳይነሱ በመሬት መንቀጥቀጡ የፈረሱት ተጨምረው የነፍስ አድን ሰራተኞችን አቅም ፈትኖታል።
የቴህራን ነዋሪዎች “ቤት ብንገባ በመሬት መንቀጥቀጥ እንሞታለን፣ አደባባይ ብንወጣ በቦምብ እንመታለን” በሚል ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ወድቀዋል።













