በአሜሪካ ጦር በቬንዙዌላ ውስጥ ሰፊ ጥቃቶች የተፈጸሙ ሲሆን ፍንዳታዎች በዋና ከተማዋ ካራከስ ውስጥ በየቦታው ታይተዋል።
ትራምፕ በማህበራዊ ሚዲያ መግለጫቸው፥ የቬንዙዌላው ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ ከባለቤታቸው ሲላ ፍሎሬስ ጋር በአሜሪካ ጦር አባላት ተይዘው ከሀገር መውጣታቸውን ገልጸዋል።
የቬንዙዌላው ፕሬዝደንት ማዱሮ አሜሪካ ውስጥ የወንጀል ክስ ተመስርቶባቸው ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ እና የተፈጸሙት ጥቃቶችም የእስር ትእዛዙን ለሚያስፈጽሙ አካላት ከለላ እና ጥበቃ ለማድረግ ሲባል የተፈጸሙ እንደነበር ሴክሬተሪ ኦፍ ስቴት ማርኮ ሩቢዮ የነገሯቸው መሆኑን የአሜሪካ ሴናተር ማይክ ሊ ለፎክስ ኒውስ ተናግረዋል።
በቬንዙዌላ የተፈጸመው ጥቃት ፕሬዝደንቱን በቁጥጥር ስር ለማዋል ያሰበ በመሆኑ፥ ከዚህ በሗላ የሚፈጸም ጥቃት እንደማይኖር ሩቢዮ የተናገሩ መሆናቸውንም ሴናተሩ ማይክ ሊ አክለዋል።
የአሜሪካ የአንድን አገር ድንበር ዘልቃ የፈጸመችው ጥቃት፥ ከብዙ አገራት እና አለም አቀፍ ተቋማት የሚሰጠው ምላሽ ይጠበቃል።
ከሳምንታት በፊት፥ አሜሪካ በካረቢያን ባህር ላይ ከቬንዜዌላ የባህር ወደብ አቅራቢያ ላይ የቬንዙዌላ ነዳጅ ጫኝ መርከብን በቁጥጥር ስር ማዋሏ እና በተመሳሳይ በሌላ ጥቃት በእጽ አዘዋዋሪነት የተጠረጠሩ ጀልባዎች ላይ የነበሩ ሰዎችን መግደሏ ይታወሳል።
አሜሪካ እና ቬንዙዌላ ላይ የገቡበት ፖለቲካዊ ፍጥጫዎች እና አሜሪካ የፈጸመቻቸውን ተከታታይ የጦር ጥቃቶች በተመለከተ የተለያዩ አስተያየቶች ይሰጣሉ።
የትራምፕ አስተዳደር፥ የማዱሮ መንግስት ወደ አሜሪካ ለሚገቡ ህገወጥ እና “አደገኛ” ስደተኞች ቀጥተኛ አስተዋጽዖ እንደሚያደርግ እና አሜሪካን መዳረሻው ያደረገ የእጽ ንግድ አንቀሳቃሽ እንደሆነ በማንሳት ይወነጅላል።
በሌላ በኩል፥ ፍጥጫው የማዱሮ መንግስት የተቆጣጠረው የቬንዙዌላ ነዳጅ ሃብት ጋር ያያይዙታል።
ቬንዙዌላ ከ300 ቢሊዮን በርሜል በላይ የሚገመት በዓለም ትልቁን የተረጋገጠ የነዳጅ ክምችት ባለቤት ስትሆን፥ ይህም እንደ ሳዑዲ አረቢያ፣ ኢራን እና ካናዳ ካሉ ሀገራት በእጅጉ ያስበልጣታል።












