የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ኡጋንዳዊ ያልሆኑ ግለሰቦችን ወደ ካምፓላ በመባረር (Deportation) ያልተለመደ እርምጃ መውሰዱን የኡጋንዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
እንደ ኡጋንዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ ከሆነ የአሜሪካ መንግስት ወደ ሀገሪቱ የላካቸው ግለሰቦች የኡጋንዳ ዜግነት የሌላቸው መሆኑ ተረጋግጧል። ይሁን እንጂ አንድ የአሜሪካ ዳኛ ግለሰቦቹ ወደ ኡጋንዳ እንዲባረሩ የሚፈቅድ ውሳኔ ማሳለፋቸው ሂደቱን እጅግ አነጋጋሪ አድርጎታል።
ይህ እርምጃ በአለም አቀፍ ስደተኞች ህግ እና በሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ላይ ትልቅ ጥያቄ አስነስቷል።
የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ወደ ሥልጣን ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ “ሕግና ሥርዓትን ማስከበር” በሚል መሪ ቃል በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን የማባረር ዘመቻውን አፋፍሞታል። የትራምፕ አስተዳደር ተግባራዊ የሚያደርገው ፖሊሲ ከዚህ ቀደም የነበሩ የጥበቃ ከለላዎችን (እንደ TPS ያሉ) በመሰረዝ ላይ ያተኮረ ነው። ይህም ብዙዎቹ ተባራሪዎች ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ ለፖለቲካዊ ስደት ወይም ለከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ እንደሚጋለጡ እየገለጹ ቢሆንም የአሜሪካ ፍርድ ቤቶች ግን ለደኅንነት ቅድሚያ እየሰጡ ይገኛሉ።

በአሜሪካ ለበርካታ ዓመታት የኖሩ ግብር የሚከፍሉና ቤተሰብ የመሠረቱ ኢትዮጵያውያን፣ ናይጄሪያውያን እና ሴኔጋላውያን ሳይቀሩ የማባረር ትዕዛዝ እየደረሳቸው ነው።
ሰሞኑን በኡጋንዳ የተከሰተው ክስተት የዘመቻውን ግድፈቶች በግልጽ ያሳየ ነው። የአሜሪካ የኢሚግሬሽን እና የጉምሩክ አስከባሪ (ICE) በርካታ ግለሰቦችን በልዩ አውሮፕላን ወደ ካምፓላ የላከ ቢሆንም የኡጋንዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ግን ግለሰቦቹ የሀገሪቱ ዜጎች አለመሆናቸውን አረጋግጧል።
የአሜሪካ ፍርድ ቤቶች እነዚህን ግለሰቦች ወደ ኡጋንዳ እንዲባረሩ የፈቀዱት ግልጽ ባልሆነ መረጃ መሆኑ፣ በዲፕሎማሲው ረገድ “ሉዓላዊነትን መጣስ” ተደርጎ ተወስዷል። ካምፓላ “የእኔ ያልሆኑትን ዜጎች አልቀበልም” በሚል አቋሟ መጽናቷ ደግሞ ግለሰቦቹን በሁለት ሀገራት መካከል “አገር-አልባ” (Stateless) አድርጎ አስቀርቷቸዋል።












