ከአፍሪካ ጋር ላለው ኢኮኖሚያዊ ትብብር ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የቻይና መንግስት፣ በአፍሪካ ሀገራት ውስጥ በሚካሄዱ የአውሮፕላን ማረፊያና ተያያዥ መሰረተልማቶች ግንባታ ላይ ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተ ነው። የቻይና የፖሊሲ ባንኮች ለበርካታ የአፍሪካ ሀገራት የአውሮፕላን ማረፊያ ማስፋፊያና ማዘመኛ የሚሆን ብድር ያበደሩ ሲሆን ግዙፍ የኮንስትራክሽን ኩባንያዎቿ ደግሞ በግንባታ ስራ ተሳትፈዋል። እነዚህ የአውሮፕላን ማስፋፊያ ፕሮጀክቶች፣ ቻይና እአአ በ2013 ይፋ ካደረገችውና በእስያ፣ በአውሮፓና በአፍሪካ የተሻለ ትስስር ለማምጣት ከሚያልመው የቻይና ቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሺየቲቭ (BRI) ጋር የሚጣጣም ነው።
ቻይና ከተሳተፈችባቸው የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች መካከል እአአ በ2019 በ363 ሚሊዮን ዶላር የተጠናቀቀው የቦሌ አለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ማስፋፊያ ፕሮጀክት በቀዳሚነት ይጠቀሳል።

ለአውሮፕላን ማረፊያ መሰረተልማቶች ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው የኢትዮጵያ መንግስት ከቻይና ባገኘው ብድር ማስፋፊያውን ገንብቶ ማጠናቀቁ ይታወሳል።መንግስት በአውሮፕላን ማረፊያ መሰረተልማቶች ላይ በየጊዜው የሚያደርገው የማስፋፊያ ስራ፣ ስመ ገናና የሆነው የኢትዮጵያ የአርመንገድ በአፍሪካ በመዳረሻና በአውሮፕላን ብዛት ያለውን የቀዳሚኒት ቦታ አስጠብቆ እንዲቀጥል አስችሎታል።
በዚህ ፕሮጀክት ላይ ቻይና ብድር በማቅረብና የግንባታ ተቋራጮቿን በማሳተፍ ወሳኝ አስተዋጸኦ አድርጋለች።ግንባታው የተከናወነው በቻይናው ግዙፍ የመሰረተልማት ግንባታ ኩባንያ (ሲሲሲሲ) ሲሆን የግንባታው 85-90 በመቶ ወጭ የተሸፈነው ከቻይና ኤክዚም ባንክ በተገኘ ብድር ነው።
ይህ ማስፋፊያ የአውሮፕላን ማረፊያውን መንገደኞች የማስተናገድ አቅም ከሶስት እጥፍ በላይ አሳድጎታል። ከማስፋፊያው በፊት ነበረው የአውሮፕላን ማረፊያው መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም 7 ሚሊየን የነበረ ሲሆን ማስፋፊያው ከተጠናቀቀ በኋላ ግን 22 ሚሊየን መድረስ መቻሉን አየርመንገዱ መግለጹ የሚታወስ ነው። ማስፋፊያው 74,000 ሜትር ስኩዬር ስፋት ያለው አዲስ ተርሚናልን፣ የመውጫ ተርሚናሎች ማስፋፊያን፣ የዘመናዊ የሻንጣ ማስተላለፊያ ስርአት ተከላን፣ ወደ አውሮፕላን መሳፈሪያ በሮችንና የጸጥታና የመንገደኞች አገልግሎት መሰረተልማቶች የማሻሻል ስራን ያካተተ ነበር። እነዚህ ማሻሻያዎች አውሮፕላን ማረፊያው ግዙፍ አውሮፕላኖችን እንዲይዝና መጨናነቅን ትርጉም ባለው እንዲቀንስ ያስቻለ ነው።
አየርመንገዱ የቦሌው አለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ማስፋፊያ ከተጠናቀቀ ከአመታት በኋላ ባለፈዉ አመት ከቻይና ጋር በመተባበር በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ የሚገኘውን የሜንቴናንስ፣ ሪፔርና ኦቨርሃውል (MRO) ህንጻ ገንብቶ አጠናቋል።

በቻይናው ሲሲሲሲ የተገነባውና 150 ሚሊዮን ዶላር የፈጀው ይህ ፕሮጀክት ዘመናዊ የሰፊ አካል አውሮፕላኖች ሃንጋሮች፣ ከፍተኛ ቴክኖሎጂ ያለው የአውሮፕላን መለዋወጫ ጥገና ማዕከል እና ዘመናዊ መጋዘን ያካትታል። ተቋማቱ በፍጥነት እያደገ ያለውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላኖች ለመደገፍ እንዲሁም የአፍሪካን ቀጣናዊ የጥገና አገልግሎት ፍላጎት ለማሟላት ታስበው መገንባታቸው ተገልጿል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው “ዛሬ ኢትዮጵያ አየር መንገድ በጥገናና ምህንድስና ዘርፉ ሶስት አዳዲስ ተቋማትን አስመርቋል። ከእነዚህም መካከል በሙሉ በራስ-ሰር የሚሠራ ዘመናዊ መጋዘን እና ሁለት የሰፊ አካል አውሮፕላኖች ሃንጋሮች ይገኙበታል። እነዚህ ተቋማት የአውሮፕላን አካል ጥገና አቅማችንን በ50 በመቶ ያሳድጋሉ” ሲሉ ነበር በወቅቱ የተናገሩት።
የፕሮጀክቱ ኃላፊዎች እንዳሉት ከሆነ ይህ ፕሮጀክት የተጠናቀቀው ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ ተግባራዊ ያልሆኑ ዘመናዊ የግንባታ ቴክኖሎጂዎች ለመጀመሪያ ጊዜ በመጠቀም ነው።
የሲሲሲሲ የቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት ዋና ሥራ አስኪያጅ ቲያን ዠንኬ “ይህ ሃንጋር 31 ሜትር የሚደርስ ከፍታ እና 90 ሜትር የሚጠጋ የአንድ ስፋት (Span) ያለው ትልቅ መዋቅር ነው። ይህን የብረት መዋቅር በአንድ ጊዜ ለማንሳት የ5ጂ የርቀት መቆጣጠሪያ ቴክኖሎጂን ለመጀመሪያ ጊዜ ተጠቅመናል። ይህ እጅግ ከባድና ፈታኝ ሥራ ነበር። ይህን ዓይነት ቴክኖሎጂ በኢትዮጵያ ለመተግበርም የመጀመሪያ ጊዜ ነው። በዚህም አዳዲስ የግንባታ ቴክኖሎጂዎችን ወደ ኢትዮጵያ ማስተዋወቅ ችለናል” ብለዋል።

ቻይና ኢትዮጵያ የአውሮፕላን ማረፊያዎቿን እንድታዘምን እንዲሁም ቀጠናዊ የአየር ትራንስፖርት መናኸሪያነቷን እንድታጠናክር ወሳኝ አስተዋጽኦ አበርክታለች። የግንባታ ስራው የአየር ትራንስፖርት አቅምን ከማሳደግ በተጨማሪም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የስራ እድል እንዲያገኙ አስችሏቸዋል።
የቻይና ኩባንያዎች መንግስት በ12.5 ቢሊየን ዶላር ከአዲስ አበባ 40 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የቢሾፍቱ ከተማ በአፍሪካ ግዙፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ማስፋፊያ ግንባታም ውስጥም በመሳተፍ ላይ ናቸው። ይህ አውሮፕላን ማረፊያ እአአ በ2030 የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታው ሲጠናቀቅ በአመት 60 ሚሊዮን መንገደኞችን የሚያስተናግድ ሲሆን ግንባታው ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ ደግም በአመት 110 ሚሊየን መንገደኞችን እንደሚያስተናግድና 270 አውሮፕላኖችን የሚያስቆም ቦታ እንደሚኖረው ተገልጿል።

ግዙፉ ሲሲሲሲ ጨረታ አሸንፎ በዚህ ፕሮጀክት ግንባታ ላይ እየተሳተፈ ይገኛል። ይህ ኩባንያ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰሩ 50 ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎችን በማስመጣት፤ በሀገሪቱ የሎጂስቲክስና ግንባታ ዘርፍ የታዳሽ ኃይልን አስተዋውቋል።
የቻይና ኩባያዎች እንዲህ ካሉ ትላልቅ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ላይ መሳተፍ፣ ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ላላት ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ትልቅ ቦታ እንደምትሰጥ የሚያሳይ ነው።በጥቅሉ ሲታይ ቻይና በኢትዮጵያ የአቪዬሽን ዘርፍ ያላት አስተዋጽኦ የሀገሪቱን የአቪየሺን ዘርፍ ትርጉም ባለው መልኩ ቀይሮታል።













