ኢትዮ ቴሌኮም በተጠናቀቀው የ2018 በጀት ዓመት (2025/26) 215.8 ቢሊየን ብር ገቢ ማግኘቱን ይፋ አደረገ። ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ33.2% እድገት ያሳየ ሲሆን ተቋሙ ካቀደው ዓመታዊ የገቢ ግብ 99.7% ማሳካቱን ያመላክታል።
የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ የዓመቱን የሥራ አፈጻጸም በተመለከተ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ በኩባንያው ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከዳታ እና ኢንተርኔት አገልግሎት የተገኘው ገቢ የጥሪ (Voice) አገልግሎትን በልጦ ከፍተኛውን ድርሻ መያዙን ገልጸዋል።

ከዳታ እና ኢንተርኔት የተገኘው ገቢ አጠቃላይ የኩባንያውን 31.1% ድርሻ በመያዝ የመጀመሪያውን ደረጃ ሲይዝ፣ የድምፅ (Voice) አገልግሎት 23.5% ድርሻ ይዟል።
አጠቃላይ የኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞች ቁጥር 90.1 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን ከዚህ ውስጥ የቴሌብር (telebirr) ተጠቃሚዎች 60.59 ሚሊዮን ደርሰዋል።
በበጀት ዓመቱ በቴሌብር 4.19 ትሪሊዮን ብር የሚያንቀሳቅሱ 2.61 ቢሊዮን ግብይቶች ተፈጽመዋል። በቀን ደግሞ 11 ቢሊዮን ብር ዝውውር ይደረግበታል። ተቋሙ በበጀት ዓመቱ 188.48 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማግኘት ችሏል።
603 አዳዲስ የሞባይል ጣቢያዎች የተገነቡ ሲሆን የ4G ሽፋን ለተጨማሪ 264 ከተሞች በመዘረጋት አጠቃላይ የ4G አገልግሎት የሚያገኙ ከተሞችን ቁጥር 1,200 (82.2% ሽፋን) አድርሷል። የ5G አገልግሎት ደግሞ በ33 ከተሞች ተስፋፍቷል።
ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ አክለው እንዳሉት፣ የያዝነው በጀት ዓመት ኩባንያው የሶስት ዓመቱን “Next Horizon” ስትራቴጂ መተግበር የጀመረበት የመጀመሪያ ዓመት ሲሆን ትኩረቱም በቴክኖሎጂ እና መሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት ላይ ያተኮረ እንደነበር ገልጸዋል።












